ቀጥታ፡

ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት እንደ ሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ አለው - የብልፅግና ፓርቲ ሰልጣኝ አመራር አባላት

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 04/2016 (ኢዜአ)፦ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት እንደ ሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ጉልህ ድርሻ እንዳለው  በሀዋሳ ማዕከል በስልጠና ላይ የሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ አመራር አባላት ገለፁ።

በሀዋሳ ማዕከል ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የብልፅግና ፓርቲ አመራር አባላት የሀዋሳን እና የይርጋለምን ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

አመራር አባላቱ እንደተናገሩት መንግስት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት እንደ ሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ነው ።

ከኦሮሚያ ክልል የመጡት አቶ ሱልጣን ሁሴን ''ፓርቲው በተለይ በ2023 ዓ.ም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን አልሞ እየሰራ ነው'' ብለዋል።

ለዚህም እንደ ሀገር ግዙፍ ኢኮኖሚን መገንባትና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ለዚህም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተተገበረ ያለው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ልማት የላቀ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

በተለይ ኢንዱስትሪዎች የሚይዙት ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነስና የአምራች ኃይሉን አቅም ጥቅም ላይ በማዋል ኢኮኖሚውን በሚገባ እንደሚያግዝ ነው የገለፁት።

ከሶማሌ ክልል የመጡት ፋጡማ መሀመድ በበኩላቸው በሀገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን የሚተኩና በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ይህም ለገቢ ምርቶች የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ በማዳንና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክተው አስተዋፅ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባደረጉት ጉብኝት ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረትና አሁናዊ እንቅስቃሴ በሚገባ መረዳታቸውን ገልፀዋል።

ፓርኩ ወደ ውጭ ከሚልካቸው በተጨማሪ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ እንዲሁም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አውታር በመሆን እንደ ሀገር ጉልህ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የአመራሩ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀው ''እየተሰጠን ያለው ሥልጠና አቅማችንን በማሰባሰብ ወደ ተግባር ለመግባትና ውጤታማ ሥራ ለመስራት የሚጠቅም ነው።'' ብለዋል ።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ የፓርኩን አጠቃላይ እንቅስቃሴን በተመለከተ ለአመራር አባላቱ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት ፓርኩ በኢኮኖሚ፣ በማህበረሰብ ተጠቃሚነት እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ላይ ውጤታማ ሥራ ለመስራት የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

በኢኮኖሚው ዘርፍ ምርቶችን ወደ ዓለም ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት በዘለለ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በሚደረገው ጥረትም ፓርኩ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ከአካባቢ ጥበቃ አንፃርም ፓርኩ “ ዜሮ ሊኩዊድ ቻርጅ ” የተሰኘ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፍሳሽ ቆሻሻ ከፓርኩ እንዳይወጣ በማድረግና ተጣርቶ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል እያደረገ እንደሚገኝም አክለዋል።

በአርባ ምንጭ፣ ሚዛንና ሆሳዕና ማዕከላት በስልጠና ላይ የሚገኙ የፓርቲው አመራር አባላትም በየአካባቢው በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በተመሳሳይም የፓርቲው ሰልጣኝ አመራር አባላት በሶማሌ ክልል በፋፈን ዞን ሸበሌና ጉርሱም ወረዳዎች የሚገኙትን የእርሻ፣ የእንስሳት እና የጂግጂጋ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም