ቀጥታ፡

አገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ የአገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲነቃቃ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል - የዘርፉ ባለሙያዎች

 አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2016 (ኢዜአ)፦  አገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ የአገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲነቃቃና የዘርፉ እድገት እንዲፋጠን ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን አገር አቀፍ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ ከቀናት በፊት በይፋ መክፈታቸው ይታወሳል።

በአውደ-ርዕዩ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሥፍራዎች፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የኪነ-ጥበብ ኃብቶችና ሌሎች መስል የዘርፉ ጸጋዎችና  አገልግሎቶች ለዕይታ ቀርበዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎች፤ የዘርፉ ባለሙያዎች፤ አውደ-ርዕዩ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኤንዲ አሰፋ፤ አውደ ርእዩ በተለይም የዘርፉን ተዋንያን አቅም የሚያጎለብት መሆኑን ገልጿል። 

እንዲሁም በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድና ለቀጣዮቹ ጊዜያትም እቅድ ለማውጣት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ተናግሯል።

አውደ ርዕዩ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለውም እንዲሁ።


 

 በኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያው ዮናስ ትኩ፤ አውደ ርዕዩ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ ያግዛል ብሏል። 

የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጾ አውደ ርእዩ ይህንን ይበልጥ በማጠናከር ቀላል የማይባል አስተዋጽዖ እንዳለው ነው ያመላከተው። 

መሰል ተግባራትን ይበልጥ በማጠናከር የዘርፉ እድገት ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግሯል። 


 

አውደ ርእዩ የዘርፉን እንቅስቃሴና የምንሰራውን ሥራ ለማስተዋወቅ አግዞናል ያለው ደግሞ የአንበሳ ትራቭል ተወካይ ፍሬው ፍስሃ ነው።

ይህም ግንዛቤ በመፍጠር የአገር ውስጥ ጎብኝዎች እንዲበራከቱ በማድረግ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብሏል። 

መስከረም 29 በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው አገር አቀፍ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ እስከ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም