የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ሕገ ወጥነትን በመቆጣጠር የጋራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ሕገ ወጥነትን በመቆጣጠር የጋራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል-ነዋሪዎች
ጋምቤላ/ጂንካ ፤ ጥቅምት 4/2016 (ኢዜአ)፡- የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ሕገ ወጥነትን ለመቆጣጠር የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጋምቤላ ከተማና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ የጋራ ስብሰባ በያዝነው ሣምንት መካሄዱ ይታወሳል ።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዜጎችን እያማረረ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ በዚህ ዓመት መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል ።
የዋጋ ንረትን ለማርገብ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ዋነኛው የመፍትሔ አካል ተደርጎ እንደሚሰራ ማመላከታቸውም እንዲሁ።
መንግሥት በ2016 የፀጥታ ስጋት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር፣ እንዲሁም ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በዘላቂነት የሚያስቀር መፍትሔ በማምጣት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ መግለፃቸው ይታወሳል።
የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መንግሥት የግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ጫናውን ለመቀነስ ከያዛቸው እቅዶች ጎን ለጎን በግብይት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታምራት ታደለ በሰጡት አስተያየት መንግሥት እያሻቀበ ያለውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በ2016 ያስቀመጠው የትኩረት አቅጣጫ ህዝቡን መሰረታዊ ችግር ያገናዘበ ነው ብለዋል።
መንግሥት ካሁን በፊትም እያሻቀበ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ሲሰራ እንደነበር ጠቁመው፣ ለችግሩ መባባስ የአቅርቦትና ፍላጎት ያለመጣጣምና በግብይት ሂደቱ የደላላ ጣልቃ ገብነት ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም መንግሥት ምርታማነትን በማሳደግ የአቅርቦትና ፍላጎትን ከማመጣጠን ባለፈ የግብይት ሄደቱን ለማስተካከል መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል።
መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ያቀዳቸውን ሥራዎች ስኬታማ ለማድረግ ወጣቱን ኃይል አስተባብሮ ወደ ልማት ሊያስገባ ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማ ነዋሪ አቶ ተሰማ ጡሙሶ ናቸው።
መንግሥት የግብርና ምርቶችን አቅርቦት ለማሳደግ የጀመረውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ኋላቀር የአመራረት ዘዴ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመቀየር ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግበትና ምርቱን ለገበያ የሚያቀርብበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት የገለፁት ሌላው በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአሪ ዞን ነዋሪዎች ናቸው።
የጂንካ ከተማ ነዋሪው አቶ በረከት ሽቺ በበኩላቸው የዋጋ ንረቱን ለማርገብ በተለይ በሕገ ወጥ ንግድ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባና እርምጃውም ጠንካራና አስተማሪ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
የአቶ በረከትን ሃሳብ አቶ ተሰማም በመጋራት የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ያሉትን የምርት መቀነስ ፣ የተዛባ የንግድ ሥርዓት፣ ተደጋጋሚ የኬላ ቀረጥና የተጋነነ የአውራጅ ጫኝ ክፍያ ችግሮች መላ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዲድሙ አግዋ በሰጡት አስተያየት እንደ ጋምቤላ ክልል ዓመቱን ሙሉ እየፈሰሰ ያለው የውሃ ሀብት ለመስኖ በማዋል እየታየ ያለውን የኑሮ ጫና ማቃለል እንደሚቻል ተናግረዋል።
አሁን ላይ እየታየ ያለውን የኑሮ ጫና ማቃለል ያልተቻለው በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ማልማት ባለመቻሉ መሆኑን አመላክተዋል።
በመሆኑም መንግሥት የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ የሥራ ባህሉን በማጎልበት አካባቢው ወደ ልማት እንዲለወጥ ለማድረግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል አቶ ዲድሙ።
የኑሮ ውድነቱን ለማስወገድ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግና ህገወጥ የንግድ አሰራሩን በግንዛቤ ማስጨበጥና አስተማሪ እርምጃን በመውሰድ ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ የሁለቱም ከተማና ዞን ነዋሪዎች በጋራ አፅንኦት የሰጡት ጉዳይ ነው።