በመዲናዋ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 4/2016 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉና የከተማዋን እድገት የሚያስቀጥሉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ በ2 ቢሊየን ብር ወጪ ያስገነባቸው ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ የቦሌ ሚካኤል ተሻጋሪ ድልድይን ጨምሮ ከአራራት ሆቴል - ኮተቤ ኮሌጅ፣ ከኮተቤ ኮሌጅ - ካራ (ሎት2)፣ ከቄራ ከብት በረት - ጎፋ መብራት ኃይል፣ ከቀጨኔ - ቁስቋም፣ ከየካ አማኑኤል ሆስፒታል - ኮተቤ እንዲሁም ሰሚት 40/60 ኮንዶሚኒየም፣ አያት 2 ኮንዶሚኒየም፣ አያት መሪ ሳይት 4 ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ፤ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለመዲናዋ ነዋሪዎች ተላልፈዋል።
እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ እድል በመፍጠርና የዜጎችን ህይወት በመለወጥ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት።
በመሆኑም ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልሱና የከተማዋን እድገት የሚያስቀጥሉ መሰል የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በመዲናዋ ከፍተኛ የካፒታል በጀት የሚመደበው ለመንገድ መሰረተ ልማት ነው ያሉት ከንቲባዋ ይህም የሆነው የመንገድ ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ ጠቀሜታ ስላለው ነው ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት 1 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጓዳኝም፤ 3 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶች መጠገናቸውንም ጠቁመዋል።
ዛሬ የተመረቁት ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች የታለመለትን የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ፣ የከተማዋን እድገት ለማስቀጠልና ገጽታ እንዲያሻሽሉ ኅብረተሰቡ የመንገዶቹን ደኅንነት በመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን በደረጃ ሊያስጠራት የሚችል ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ላይ እያደረገ ያለው ሥራ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት የመንገድ ፕሮጀክቶች ለከተማዋ ትራንስፖርት መሳለጥ ከሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ጎን ለጎን አዲስ አበባን ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም ለትራፊክ መሳለጥ ማነቆ የሆኑ አካባቢዎችን ነቅሶ በማውጣት ተገቢውን የማሻሻል ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያከናውን ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ፤ ባለሥልጣኑ በ2016 በጀት ዓመት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በእርጅና ምክንያት የተጎዱ የመንገድ ክፍሎችን ሰፋፊ ጥገናዎች በማከናወን የአገልግሎት ጊዜያቸውን ማራዘም ሌላኛው የባለሥልጣኑ ተግባር መሆኑንም እንዲሁ።