ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ሥልጠና ተሳታፊዎች በከንባታ ዞን የተከናወኑ የስንዴ የልማት እና የሌማት ቱሩፋት ስራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 4/2016 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ማዕከል 2ኛ ዙር የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ሥልጠና ተሳታፊዎች በከንባታ ዞን የተከናወኑ የኩታገጠም ስንዴ ልማት እና የሌማት ቱሩፋት ስራዎችን ጎብኝተዋል። 

 የአመራር ሥልጠና ተሳታፊዎችም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ሲሆን፥ በከምባታ ዞን የተከናወኑ የኩታገጠም ስንዴ ልማት እና የሌማት ቱሩፋት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። 

በጉብኝቱም የኩታገጠም ስንዴ ምርታማነት፣ በሌማት ቱሩፋት የተገኙ ስኬታማ የወተት ላም እርባታ፣ የስጋ ዶሮ እና እንቁላል ልማት ሥራዎች የዜጎችን ህይወት በማሻሻል ከፍተኛ ውጤት እንደተገኘባቸው ተገልጿል። 

በከምባታ ዞን ከ6ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በስንዴ ሰብል መልማቱን ተመላክቷል።


 

በሌማት ቱሩፋት ኢኒሸቲቭም ከስጋ ዶሮና እንቁላል ምርታማነት በተጨማሪ በወተት ላም ማዳቀል ስራ ከአንድ ላም በአማካይ በቀን ከ16 ሊትር በላይ  የወተት  ምርት እየተገኘ መሆኑ ተገልጿል። 

የሌማት ቱሩፋት ኢንሸቲቭም የአካባቢውን ማህበረሰብ አመጋገብና ሥነ-ምግብ  ሥርዓት በማሻሻል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተመላክቷል። 

በጉብኝቱም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የተውጣጡ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ የከምባታ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም