የግል ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪን የሚያድኑ የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ በመሳተፍ ኢኮኖሚውን ሊደግፉ ይገባል - ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
የግል ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪን የሚያድኑ የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ በመሳተፍ ኢኮኖሚውን ሊደግፉ ይገባል - ዶክተር አለሙ ስሜ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2016(ኢዜአ)፦ የግል ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሬን የሚያድኑ የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ በመሳተፍ ኢኮኖሚውን ሊደግፉ ይገባል ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአይሱዙ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፣ ሽያጭና ድህረ ሽያጭ ማዕከል ዛሬ ተመርቋል።
ሚኒስትሩ በምረቃው ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት አምስት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ በሁሉም መስክ በቀጣይነት ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ቢሆንም የሎጅስቲክስ አፈፃፀማችን ዝቅተኛ ነው።
በመሆኑም የጭነት ተሽከርካሪዎች በብዛት እንዲመረቱ በማድረግ የሎጅስቲክስ ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚያስፈል አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የውጭ ምንዛሪን ለማዳን የአገር ውስጥ ምርቶች ተመራጭ በመሆናቸው የግል ባለሃብቶች በዘርፉ በመሳተፍ ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴርም የአገር ውስጥ አምራቾችን እንደሚያበረታታ ገልፀዋል።
በአገሪቱ የመጀመሪያ እንደሆነ የተነገረለት የጃፓን ስሪት የሆነ የአይሱዙ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ፣ የሽያጭና ድህረ ሽያጭ ማዕከል ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ሀገራዊ ኢኮኖሚን ከመደገፍ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
ማዕከሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የካኪ ሞተርስ የግል ኩባንያ ስራ አስፈፃሚ አቶ ገብረሚካኤል ግርማይ ናቸው።
በአለም ገና ከተማ የሚገኘው ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ሲሰራ በዓመት 2 ሺህ 500 የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንደሚያመርት መገለጹን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ፣ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡