ሀረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ሀረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2016 (ኢዜአ)፡- ሀረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት ከተማ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ባህል ፣ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበጀት አመቱ ትኩረት ተሰጥቶ በሚሰራባቸው ዋነኛ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ሀረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እና ለቱሪስቶች አመቺ እንድትሆን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከተማዋ ህያው የሆኑ ሙዚየሞች ያቀፈች በመሆኑ የቱሪዝም ብራንድ (ሎጎ) ተቀርፆ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
የጅብ ትርኢት ማሳያ ስፍራን ለቱሪስቶች ምቹ ማድረግ የሚያስችል ኢኮ ፓርክ ግንባታ በዘመናዊና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሰራት ወደ ስራ ተገብቷል ያሉት የቢሮ ሃላፊው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ከጅብ ማብላት ትርኢት ባሻገር የቱሪዝም ፍሰቱን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በበጀት አመቱ ጉዳት የደረሰባቸው 6 ባህላዊ ቤቶች እና 2 ጥንታዊ አድባራት ቅርሱን እና ይዘቱን ሳይለቅ የማደስ ስራ ይሰራል።
በአለም ቅርስነት የተመዘገበው ጀጎል አለም አቀፍ ቅርስንና ሌሎች ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ቅርሶችን ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉም ይሰራል ብለዋል፡፡
የህዝቦች አብሮነትንና አንድነት የሚያጎለብቱ እና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ስራዎች እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።
በሌላ በኩልም የማይዳሰሱና ቱባ ባህሎች እና ቅርሶችን ለትውልድ እንዲተላለፉ የሚያስች ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባሻገርም በክልሉ የሚገኘው ሸሪፍ የግል ሙዚየምን የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የሐረሪ ቋንቋ ለማጎልበትም እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሙዚየሞችና ሌሎች የመስብ ስፍራዎች ምቹ እንዲሆኑ እሴት በመጨመር በትኩረት ይሰራሉ ብለዋል።
በዘርፉም የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲጎለብትም እየተደረጉ ርብርቦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት አቶ ተወለዳ የክልሉ ነዋሪም ቅርስን በመጠበቅና እየተሰሩ በሚገኙ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ተግባራት ድጋፉን እንዲያጠናክር መጠየቃቸውን ከሀረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡