መምህራን በእውቀትና ሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የሚካሄደውን የተቀናጀ ሥራ ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
መምህራን በእውቀትና ሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የሚካሄደውን የተቀናጀ ሥራ ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬደዋ ፤ጥቅምት 3/ 2016 (ኢዜአ)፡- መምህራን በእውቀትና ሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በሚካሄደው የተቀናጀ ሥራ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ዓለምአቀፍ የመምህራን ቀን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ውይይቶች ዛሬ ተከብሯል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉትን የትምህርት ጥራትና ውጤት ማጣት ችግሮች ለመፍታትና የተሻለ ለውጥ ለማስመዝገብ አዲስ የአጠቃላይ ሥርዓተ - ትምህርትና የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
በድሬዳዋ አስተደደር አዲሱ የትምህርት ሥርዓት አምና በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤ ዘንድሮ ወደ ሙሉ ትግበራ መሸጋገሩን ጠቁመዋል።
አዲሱ የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓት ለትምህርት ጥራትና ውጤት ማጣት መሠረታዊ ምክንያቶች መፍትሄ እንደሚሰጥ ያመለከቱት ከንቲባው፤ በትምህርት ውጤታማ የሆኑና በሥነ ምግባር የታነፁ ትውልዶች ለማፍራት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በተለይ መምህራን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው በመስራት በዕውቀትና ክህሎት የበሰለ አገር ተረካቢና ገንቢ ትውልድ ለማፍራት የሚካሄደውን የተቀናጀ ስራ ውጤታማ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ዘንድሮ በትምህርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያግዙ መሠረታዊ ስራዎች በህዝባዊ ንቅናቄ ተከናውነዋል።
የብየ አዋሌ የገጠር ትምህርት ቤት ርዕሰ- መምህር ጌቱ ቦጋለ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የአስተዳደሩ ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋል። በተጨማሪም መምህር፣ ተማሪና ወላጅ ዘላቂ አንድነት እንዲፈጥሩ ማድረግ ይገባል።
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የተቀናጀ ስራ መስራትና ለውጤት መረባረብ የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ያሉት ደግሞ ለ33 ዓመታት አስተምረው በጡረታ የተሰናበቱት መምህርት አሚና መሐመድ ናቸው።
በዓለምአቀፍ የመምህራን ቀን የገጠርና ከተማ መምህራን የተሳተፉ ሲሆን፤ በዘንድሮ ዓመት በትምህርት ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ቃል ገብተዋል።