ቀጥታ፡

የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ እምቅ የቱሪዝም ኃብቶችን ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያግዝ ነው- ቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2016(ኢዜአ)፦ ሀገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ እምቅ የቱሪዝም ኃብቶችን ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያግዝ መሆኑን ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ ከቀናት በፊት በይፋ መክፈታቸው ይታወሳል።

በአውደ-ርዕዩ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሥፍራዎች፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የኪነ-ጥበብ ኃብቶችና የዘርፉ ተዋንያን አገልግሎቶች ለዕይታ ቀርበዋል።

የአውደ-ርዕዩን ዓላማና የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ በተመለከተ ኢዜአ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የአውደ-ርዕዩ ዓላማ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም ኃብቶችን፣ የማኅበረሰቡን ታሪክና ልዩ ልዩ ባህሎች ለማስተዋወቅ መሆኑን ገልፀዋል።

በየክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ኃብቶች የሚተዋወቁበት፣ የቱሪዝም አገልግሎት ላይ የሚሰሩ ተቋማት የሚገናኙበትና በቴክኖሎጂ የታገዘ የዘርፉ አገልግሎት የሚታይበት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአውደ-ርዕዩ ልዩ ልዩ ሁነቶችና የውይይት መድረኮች የሚካሄዱበት ሲሆን፤ ከመድረኮቹ መካከል የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ፎረም አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የተዘጋጀው ሁነት በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ከተሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠሪያ መሆኑንም ገልፀዋል።

በቱሪዝም ዘርፉ ያሉ እምቅ ኃብቶችን ለመጠቀምና ማነቆዎችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል።

የአፋር ክልልን የቱሪዝም ኃብቶች ለማስተዋወቅ የተገኙት ኖራ ጁሃር፤ መድረኩ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ለማግኘትና በዘርፉ ከተሰማሩ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።


 

አውደ-ርዕዩን ሲጎበኙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሰላማዊት አስደግድግ፤ በሁነቱ በርካታ የሀገሪቷን ኃብቶች የተመለከትኩበት ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም የቱሪዝም ኃብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የተሻለ ገቢ ለማግኘት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው ሀገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ ለአንድ ወር ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም