የወባ በሽታን በዘላቂነት ለመከላከል ልዩ ትኩረት ተደርጓል - የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
የወባ በሽታን በዘላቂነት ለመከላከል ልዩ ትኩረት ተደርጓል - የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ

አሶሳ፤ ጥቅምት 3/2016(ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ የወባ በሽታን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመግታት ስትራተጂ ተነድፎ እየተሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
አምስተኛው ሀገር አቀፍ የወባ ሳምንት ዛሬ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን መንጌ ወረዳ ተከብሯል።
ሚኒስትሯ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በ2015 የበጀት ዓመት ወባ ለመከላከል በሃገሪቱ 537 ወረዳዎች ከ19 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ አጎበር ተሰራጭቷል ብለዋል።
ከ1 ሚሊዮን በሚበልጡ ቤቶች ላይ የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት መካሄዱን እና በቂ የበሽታው መመርመሪያ "ኪቶች" ለክልሎች መሠራጨታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከ40 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ 13 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ምርመራ ተደርጎላቸው ከመካከላቸው ሶስት ነጥብ አንድ ሰዎች በሽታው እንደተገኘባቸው ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።
ይህም ከ2014 በጀት ዓመት ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሮ መገኘቱን አመላክተዋል።
ሚኒስቴሩ በሽታውን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመግታት ስትራቴጅ ነድፎ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶክተር ሊያ ፤ በአሁኑ ወቅት የክረምቱ መውጣት ተከትሎ አካባቢ ጽዳት እና ተያያዥ የወባ መከላከል ስራ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው፤ አንድ ሃገር አምራች ዜጋ የሚኖረው ጤንነቱ የተጠበቀ ትውልድ ሲኖር መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወባና ሌሎችም በሽታዎችን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
"ወባን መከላከል ከእኔ ይጀምራል" በሚል መሪ ሀሳብ በተከበረው የወባ ሳምንት መርሀ ግብር ላይ የክልሎች ጤና ቢሮ ሃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።