ቀጥታ፡

የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2016 (ኢዜአ)፦ የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የተርባይኑ ጥገና ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን የጣቢያው ስራ አስኪያጅ ብሩክ ኤባ ገለጹ።

የኃይል ማመንጫ ጣቢያው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ኢዜአ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም መዘገቡ ይታወሳል። 

ከግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ጣቢያው ኃይል የማመንጨት ተግባሩን በግማሽ ቀንሶ እየሰራ እንደነበርም በዘገባው ተመላክቷል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ስራ አስኪያጅ ብሩክ ኤባ፤ አሁን ላይ የኃይል ማመንጫ ተርባይኑ በመጠገኑ በሙሉ አቅሙ ሃይል በማመንጨት ላይ ነው ብለዋል።

ከጥር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ የኃይል ማመንጫ ተርባይኑ ላይ መጠነኛ ብልሽት ገጥሞት ከአንድ አመት በላይ ኃይል የማመንጨት ስራውን አቋርጦ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኃይል ማመንጫ ተርባይኑን ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት የመለዋወጫ እጥረት ገጥሞ የነበረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከመስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ግን ተርባይኑ ተጠግኖ በሙሉ አቅሙ ኃይል እያመነጨ ነው ብለዋል።

የሰራተኛውን አቅም በመጎልበትና የመለዋወጫ አቅርቦቱን በማሟላት የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረትና ቆሻሻ የማቃጠል ተግባሩን መቀጠሉንም ገልጸዋል። 

የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር በመዲናዋ በቀን በአማካይ ከሚሰበሰበው 2 ሺህ 500ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ 1 ሺህ 280 ቶኑን እንዲቃጠል እያደረገ ይገኛልም ብለዋል። 

በ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የተገነባው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ 2011 ዓ.ም በሙከራ ደረጃ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም