ቀጥታ፡

የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የተሟላና ጠንካራ ዝግጅት በማድረጋቸው ታላላቅ ሁነቶች ያለምንም የጸጥታ ችግር ተከብረዋል - የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2016 (ኢዜአ)፦የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የተሟላና ጠንካራ ዝግጅት በማድረጋቸው በመስከረም ወር ታላላቅ ሁነቶች ያለምንም የጸጥታ ችግር መከበራቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የመስከረም ወር በርካታ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ ክብረ-በዓላት፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በአዲስ አበባና በመላው ሀገሪቱ  የተከናወኑበት ነው።

እነዚህ በርካታ ሕዝብ፣ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችና ባለሥልጣናት ጭምር የታደሙባቸው ሁነቶች በሰላም  መከናወናቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ፤ በዓላቱ በፀጥታ አካላት ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር በሰላም ተከብረዋል ብለዋል።

ለኢትዮጵያ የገፅታ ግንባታ የጎላ ፋይዳ የነበራቸው እነዚህ ሁነቶች ያለምንም ችግር እንዲከበሩ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ በቂ ዝግጅት በማድረግ ተልዕኳቸውን በብቃት መፈፀማቸውን ጠቅሰዋል።

የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ላይ በቴክኖሎጂ፣ በሎጂስቲክስ እና በሰው ኃይል የተደረገው የሪፎርም ሥራም ስኬት ማምጣቱን ያሳየ ነው ብለዋል።

ሪፎርሙ በዓላትና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች በሰላም እንዲካሄዱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የፀጥታና ደኅንነት ተቋማቱ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ እመርታ እያስመዘገቡ እንደሆነ የተግባር ምስክር ሆኗል ነው ያሉት።

የደኅንነትና የመረጃ ተቋማት ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት መረጃዎችን በመተንተን የኦፕሬሽን ኃይሉ አስተማማኝ እርምጃ በመውሰድ ስጋቶችን አስቀድሞ እንዲቆጣጠር የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን በመስከረም ወር በተከናወኑ ሁነቶች አረጋግጠናል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ።         

የፀጥታና ደኅንነት  የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመስከረም የተካሄዱ ሁነቶችን በሚመለከት አስቀድሞ ባደረገው የስጋት ግምገማ  ዓላማቸውን በኃይል ማሳካት የሚፈልጉ ጽንፈኛ ኃይሎች እንደነበሩ ማረጋገጡን አውስተዋል።

በዓላቱን በሰላም በማክበር፣ የአካባቢውን ደኅንነት በማስጠበቅና መረጃዎችን ለፀጥታ ተቋማት በመጠቆም የኅብረተሰቡ ትብብርና ተሳትፎ የላቀ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በበዓላቱ ላይ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸው መልዕክቶች እንዳይተላለፉ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና ወጣቶች ያደረጉት አስተዋጽዖ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ብቻ በየአካባቢው ከ2 ሺህ 400 በላይ የደመራ ሥነ-ሥርዓቶች፣ በአድባራት 250 የደመራ ሥነ-ሥርዓት ያለምንም ችግር መከበሩን አስታውሰዋል።

በመሰቀል አደባባይ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብና የውጭ ሀገራት ዜጎች በተገኙበት እሴቱን ጠብቆ በተረጋጋና በሰላም መከበሩንም እንዲሁ።

በሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀርሰዲ ከ7 ሚሊየን በላይ ሕዝብ የተሳተፈበት የኢሬቻ በዓል በሰላም ተከብሯል ብለዋል።

በመስከረም የተከናወኑ ታላላቅ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በሰላም መከናወናቸው ለቀጣይ የተልዕኮ አፈጻጸም ልምድ የተወሰደበት መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ገልፀዋል።

በተለይም የስጋት ሁኔታዎችን በሚገባ በመተንተን ለመቀልበስ የሚያስችል ትልቅ ልምድና አቅም የተፈጠረበት ነው ብለዋል።

በቀጣይም በርካታ ሕዝብ የሚታደምባቸው የአደባባይ በዓላት፣ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔና ሌሎችም ታላላቅ ሁነቶች በሰላም እንዲከናወኑ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም