ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የምርት ብክነትን ለመቀነስ ትኩረት ባደረገ መልኩ የመኸር አዝመራ መሰብሰብ ተጀምሯል -- የክልሉ ግብርና ቢሮ

አዳማ ፤ ጥቅምት 3/2016 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የምርት ብክነትን ለመቀነስ ትኩረት ባደረገ መልኩ የመኸር አዝመራ መሰብሰብ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ ።

የ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን የመኸር አዝመራ በዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች በመታገዝ ምርቱን የመሰብሰብ ስራ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳአ ወረዳ ቃጥላ ቀበሌ ትናንት በይፋ ተጀምሯል።


 

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት በዘንድሮው የመኸር አዝመራ 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ለ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ለማልማት የታቀደ ቢሆንም   በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ መሬቶችን ወደ እርሻ በማስገባት 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በመኸር እርሻ መልማቱን አንስተዋል።


 

በዚህም 265 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን የገለፁት አቶ ሙስጠፋ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ቆላማና ወይና ደጋ የአየር ሁኔታ ባላቸው አካባቢዎች ስንዴ፣ ጤፍና ሌሎች ሰብሎች በመካናይዜሽን በታገዘ መልኩ ሰብል መሰብሰብ ተጀምሯል ብለዋል።

''በምስራቅ ሸዋ ዞን አደኣ ወረዳ ቃጥላ ቀበሌ በመካናይዜሽን በመታገዝ የደረሰውን ሰብል የመሰብሰብ ስራ ጀምረናል'' ያሉት ዳይሬክተሩ የደረሰውን ሰብል ለመሰብሰብ በክልል ደረጃ 567 ኮምባይነሮች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የምርት ብክነትን ለመቀነስ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ሙያዊ ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን አመልክተዋል።



የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው በዞኑ በመኸር አዝመራ ስንዴን በስፋት በክላስተር ማልማት ተችሏል ብለዋል።

''ከዚህ በፊት በዞኑ አዳኣ ወረዳ ቃጥላ ቀበሌ የኩታ ገጠም እርሻና በመካናይዜሽን የታገዘ ግብርና አይታወቅም'' ያሉት አቶ አባቡ ዘንድሮ በቀበሌው 2 ሺህ 189 ሄክታር መሬት አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ስንዴ ብቻ በማልማት በካምባይነር እየታጨደ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርት ዘመን በዞኑ ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በዋና ዋና ሰብሎች እንጠብቃለን  ያሉት አቶ አባቡ አርሶአደሩ በአጨዳ ወቅት ኮምባይነር በማግኘቱ የምርት ብክነትን ከመቀነስ ባለፈ ጊዜና ወጪን እየቆጠበላቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አብነት ዘገየ በበኩላቸው በዞኑ ከ515 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ጤፍና ስንዴን ጨምሮ በዋና ዋና ሰብሎች መልማቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የደረሰውን ሰብል በመከናይዜሽንና በሰው ጉልበት የመሰብሰብ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በመኽር አዝመራ ከለማው መሬት ውስጥ 245 ሺህ ሄክታር በስንዴ ብቻ የለማ መሆኑን አቶ አብነት ተናግረዋል።

'8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ  አጨዳ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ቦሎቄ፣ ማሾ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎና ሌሎች የደረሱ ሰብሎች እየተሰበሰቡ መሆኑን አመልክተዋል።

የአዳኣ ወረዳ ቃጥላ ቀበሌ አርሶ አደር ሰይፉ ገረሱ፣ ሶስት ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በስንዴ በማልማት 144 ኩንታል ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

ምርቱን በኮምፓይነር በመሰብሰባቸው ጊዜና ወጪያቸውን ከመቆጠብ ባለፈ የምርት ብክነትን ከመቀነስ አኳያ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም