ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ የባለ ብዙ ወገን የትብብር ግንኙነትን የሚከተልና ከምንም በላይ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም ነው - የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ የባለ ብዙ ወገን የትብብር ግንኙነትን የሚከተልና ከምንም በላይ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስትራቴጂ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተርና ተመራማሪ ጃፋር በድሩ ገለጹ።  

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ የመንግሥትን ዓመታዊ የትኩረት አቅጣጫ የተመለከተ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም በ2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ትልቁ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርህ ወዳጅነትን የማብዛት፣ አጋርን የማበራከትና የልማት አጋሮችን የማቀፍ በመሆኑ በዚሁ መልክ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ለኢዜአ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፤ የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል በብዙ መልኩ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር የዲፕሎማሲ ስኬት ስለመሆኑም አንስተዋል።

በባለ ብዝኃ-ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የኢትዮጵያን ተደማጭነት ከፍ ከማድረግ ባለፈ የአፍሪካን ድምፅ በዓለም እንድታስተጋባ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል። 

ኢትዮጵያ የልማትና የኢኮኖሚ የትብብር አማራጯን በማስፋት ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ የባለ ብዙ ወገን ተቋማትን መቀላቀሏ ጉልህ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ የባለ ብዙ ወገን የትብብር ግንኙነትን የሚከተልና ከምንም በላይ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም መሆኑን ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑንም አስረድተዋል። 

የፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ንግግርም ኢትዮጵያ የባለ ብዝኃ-ወገን ዲፕሎማሲ መርህን መከተሏ በፍትሃዊነት መቆምን የሚያስረዳ ስለመሆኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ወዳጅን የማብዛትና አጋሮችን የማበራከት የዲፕሎማሲ መርህ የጋራ ተጠቃሚነትንና የትብብር ግንኙነትን መሠረት ያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም