የመማር ማስተማሩን ስራ በተቀናጀ አግባብ በመምራት ውጤታማ መሆናቸውን የሶስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች አስታወቁ

ደሴ/ አዳማ/ሆስዕና፤ ጥቅምት 3 /2016 (ኢዜአ)፡- የመማር ማስተማሩን ስራ  በተቀናጀ አግባብ በመምራት ተማሪዎቻቸውን ለከፍተኛ ውጤት ማብቃታቸውን የደሴ ፣የአዳማና የሊች ጎጎ  አዳሪ ትምህርት ቤቶች የስራ ሃላፊዎች   አስታወቁ።

በ2015 ዓ.ም በተሰጠው የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎቻቸውን ያስፈተኑት የእነዚህ ትምህርት ቤቶች የስራ ሃላፊዎች እንዳሉት፤ ተማሪዎቻቸው በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ ብርቱ ክትትልና ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል። 

የይሁኔ ወልዱ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ኃይሌ ፤በትምህርት ቤቱ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህም ስራ ተማሪዎች በቴክኖሎጅ ታግዘው ትህርቱን እንዲከታተሉ በማድረግ የትምህርት ጥራቱን ከማረጋገጥ ባለፈ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል።

የመማር ማስተማሩን ስራ በተቀናጀ አግባብ በመምራት በ2015 ዓ.ም የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተናን የወሰዱ 53 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ የዩኒቨሲቲ መግቢያ  ውጤት በማስመዝገብ ማሳለፍ እንደቻሉ አሰረድተዋል።

ትምህርት ቤቱ ካስፈተናቸው ተማሪዎች መካከል 11  ሴቶች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ፈተናውን ከወሰዱት መካከልም 16ቱ ከ600 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ፣  የደሴ ከተማ አስተዳርና አማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ክትትል፣ ቁጥጥርና የተቀናጀ ድጋፍ መስጠታቸው  የተሻለ ውጤት እንዲሚዘገበ አስተዋጽወዋቸው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ የባዮሎጂ መምህር አማረ ሰጤ በበኩላቸው፤ ከመምህራንና ተማሪዎች የጋራ ጥረት በተጨማሪ የተማሪዎች የማወቅ ጉጉት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አስችሏል ብለዋል፡፡

የትምህርት ጥራቱን በማረጋገጥ ይህ መልካም ስም እንዲቀጥል በቴክኖሎጂ የታገዘ መማር ማስተማር ሥራችንን በቅንጅት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅር አበበ ፤  እንደ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዓይነት ሞዴል ትምህርት ቤቶችን የማስፋት ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።


 

ለዚህም ለዘንድሮው በጀት ዓመት  7 ሚሊዮን ብር በመመደብ የተሻለ ውጤት ያላቸውን 320 ተማሪዎች በመምህር አካለ ወልድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስተማር መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ተማሪዎች ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ልዩ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ቀጣይ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ሙሉ በሙሉ እንዲልፉ ይሰራል ብለዋል።

በሂደትም ትምህርት ቤቱን ሙሉ በሙሉ ሞዴል ትምህርት ቤት ለማድረግ ታቅዷል።

የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ፈተና ወስደው በክልሉ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 100 አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ልማት ማህበር የአዳማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ አበበ ዘውዴ እንደገለጹት፤ በ2015 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ 99 ነጥብ 3 በመቶው 400 እና ከዛ በላይ ውጤት አምጥተዋል።


 

ከትምህርት ቤቱ ለፈተና ከተቀመጡት 144 ተማሪዎች  20ዎቹ ከ600 በላይ ሲያመጡ፤  በትምህርት ቤቱ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 637 መሆኑን አስታውቀዋል።

ከ400 በላይ ውጤት ያመጡት ደግሞ 143 ናቸው ብለዋል።

ለውጤቱ መሳካት ተማሪዎችን በቅርበት በመከታተልና በመደገፍ  ለጥናት በቂ ጊዜ መስጠትና የትምህርት ክፍለ ጊዜ በአግባቡ መምራት በመቻሉ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ተማሪዎቹ ከቤተሰብ ተለይተው በትምህርት ቤቱ በመማር ማስተማር ላይ የሚገኙ በመሆናቸው  ስነ ልቦና ግንባታ ላይ ከ10 እስከ 15 ተማሪ በአንድ አስተማሪ ስር በማደራጀት የምክርና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት ሌላው ምክንያት እንደሆነ አንሰተዋል።

ሶስት ጊዜ ሞዴል ፈተና በመስጠት የተማሪዎች ውጤት ምዘናና ግምገማ በማድረግ ክፍተቶች በፍጥነት መሙላት፣ የተቀናጀ  ተግባር ተኮረ የመማር ማስተማርና ሌሎችም ግብአቶች  ማደራጀት መቻሉ ውጤታማ ለመሆን እንዳበቃቸው አመላክተዋል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሊች ጎጎ ልዕቀት ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ተከተል ሱሞሮ በበኩላቸው፤  የተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ አሰራሮችን በመዘርጋትና የመማር ማስተማር ስራ በቅንጅት በመምራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ከትምህርት ቤቱ በ 2015ዓ.ም  ለ12ኛ ክፍል ፈተና  35 ተማሪዎችን  ፈተና ላይ በማስቀመጥ በከፍተኛ ዉጤት ሙሉ በሙሉ  ማሳለፋቸውን  አስታውቀዋል።

ከክፍል ውስጥ ትምህርት በተጨማሪ በተግባርና በቴክኖሎጂ የተደገፈ  የተቀናጀ   የመማር ማስተማር ስራን በመከተል ተማሪዎቹን ለከፍተኛ ውጤት ማብቃት እንደተቻለ አስረድተዋል።

የተገኘውን ውጤት አስጠብቆ በማስቀጠል  በራሳቸው  የሚተማመኑ የበቁ ዜጎችን በማፍራት ተቋሙን የልዕቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።  

የሀድያ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አድነው ሎንሰቆ በሰጡት አስተያየት  ፤ በልማት ማህበሩ ስር የሚተዳደረው የሊች ጎጎ ልዕቀት ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት በእውቀት የበቁ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለሀገር ማበርከት ዋነኛ ዓላማው ነው ብለዋል።  

ለዚህም ተወዳዳሪ የሆኑ ብቁ መምህራን በማመቻቸትና አስፈላጊ  የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላት አመርቂ ውጤት እንዲመዘገብ የልማት ማህበሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም