የሐሳብ ልዮነቶቻችንና አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር መፍታት ያስፈልጋል- ዶክተር አይሮሪት መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
የሐሳብ ልዮነቶቻችንና አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር መፍታት ያስፈልጋል- ዶክተር አይሮሪት መሐመድ
ሰመራ ፤ ጥቅምት 2/2016(ኢዜአ) ፡- "የሐሳብ ልዮነቶቻችንና አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር መፍታት ይኖርብናል'' ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ ገለፁ።
ኮሚሽኑ በሰመራ ከተማ በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ አካላትን ለመመልመል የሚያግዙ ተባባሪ አካላትን ለሶስት ቀናት ለማሰልጠን ያዘጋጀውን መርሃ ግብር ዛሬ ተጠናቋል።
ኮሚሽነሯ በዚሁ ወቅት እንዳሳሰቡት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የውይይት ባህላችንን ማዳበርና ማጠናከር ያስፈልጋል።
የአፋር ሕዝብ የግጭት መፍቻ እሴቶች እንዳሉት ገልጸው፣ እሴቶቹን በሥራ ላይ በማዋል ችግሮቻችን ለመፍታት መጠቀም ይገባናል ብለዋል።
ስልጠናውን የወሰዱ ተባባሪ አካላት በቀጣይ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የማህበረሰብ አባላትን በመለየት ሚና እንዲጫወቱ ዶክተር አይሮሪት አሳሰበዋል።
ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከደዌ ወረዳ የመጡት አቶ አሊ መሐመድ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉንን የሐሳብ ልዩነቶቻችንን ወደጎን በመተው በውይይትና በምክክር ችግሮቻችንን መፍታት ይገባናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትደርስ በውይይትና በምክክር የሚያምን ትውልድ እንዲፈጠር ማህበረሰቡ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ከአሚባራ ወረዳ የመጡት ሊቀ ብርሃን ላዕከ ማርያም በሰጡት አስተያየት ሀገራዊ ምክክሩ እየተስተዋለ ያለውን አለመግባባት የሚያስቀርና አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ የሚያስቀምጥ እንደሆነ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
''ምክክር ካለ መፍትሄ ይመጣል፤ እንመካከር የሚል አካልና የሚመካከርና የሚቀራረብ ህዝብ ውጤታማ ይሆናል'' ያሉት ደግሞ ከአብአላ ከተማ አስተዳደር የመጡት አቶ አብደላ ኢላልታ ናቸው።
''ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ላይ ቁጭ ብለን መነጋገር ከተቻለ፤ ውጤትም ሊመጣ ይችላል'' ብለዋል።
በመወያየትና በመመካከር የሚያምን ትውልድ እንዲፈጠር አሻራ ማስቀመጥ ይኖርብናል ያሉት ደግሞ ከተላላክ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ፋጡማ ዓሊ ናቸው።
የምክክርና የውይይት ባህል በአፋር ብሎም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
''ሀገራዊ ምክክሩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ያግዛል'' ሲሉ የተናገሩት ደግሞ ከአርጎባ ልዩ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ሷሊህት አህመድ ናቸው።
ስልጠናውን ከአፋር ክልል 48 ወረዳዎች የተውጣጡ 432 ተባባሪ አካላት ተሳትፈውበታል።