ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አብነት የሚሆን ስራ እያከናወነች ነው-ክሪስ ኒኮይ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 02 / 2016(ኢዜአ)፡ - ኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አብነት የሚሆን ስራ እያከናወነች መሆኑን በዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክሪስ ኒኮይ ገለፁ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክሪስ ኒኮይ  በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ  እና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ደጃዝማች ወንድይራድ የመጀመሪያ  ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር አተገባበርን ተመልክተዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክሪስ ኒኮይ በዚሁ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር የመጪው ዘመን የትውልድ ኢንቨስትመንት መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

ይህም ብቁ ትውልድ ከመፍጠር ባሻገር ለኢትዮጵያ ቀጣይ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በምግብ ምርቶች ግብይት ሰንሰለትን በማጠናከር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም እንዲሁ፡፡

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት ለመርሃ ግብሩ ትግበራ የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ኢትዮጵያ መርሃ ግብሩን በራሷ የፋይናንስ አቅም እየተገበረች መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት የሚደነቅ ስራ እያከናወነ መሆኑን አንስተው፤ መርሃ ግብሩ ለህጻናት ተማሪዎች ስኬታማነት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤ በመዲናዋ ከ800 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የቅድመ አንደኛ ፣ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

መርሃ-ግብሩ በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፤  በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡ 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም