ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከር ያስችላል -በአፋር ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከር ያስችላል -በአፋር ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች
ሰመራ፤ ጥቅምት 2/2016(ኢዜአ) ፡- ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከር የጎላ ሚና እንደሚኖረው በአፋር ክልል የማህበረሰብ ተወካዮች ተናገሩ።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሠመራ ከተማ እያካሄደ በሚገኘው ውይይት በቀጣይ ለሚካሄደው ምክክር በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ አካላት በመመረጥ ላይ ናቸው።
ከዳሎል ወረዳ ለአጀንዳ ልየታ የተመረጡት አቶ ዓሊ መሐመድ፣ ሀገራዊ ምክክር ሀገር ለገጠሟት ችግሮች የጋራ መፍትሄ ለማፈላለግና ሰላም ለማስፈን ይረዳል ብለዋል።
የኮሚሸኑን ተልዕኮ በማሳካት ኃላፊነታቸው ለመወጣትም ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ አንድነትን ከማጠናከር አልፎ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከር አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
አቶ ከድር ጣሂር የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው ኮሚሽኑ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሐሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነና በዘመናዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ግንዛቤ የጨበጡበት መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሸነር አቶ ሙሉጌታ አጎ፣ ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውና አስጠብቆ ለማቆየት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን ተከባብሮና ተፋቅሮ የመኖር ባህል ያጠናክራል፤ የአገር ግንባታን ያጎለብታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በዚህ ሣምንት ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክሩ መጀመር መሰረታዊና ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።