ቀጥታ፡

ብሔራዊ ተኃድሶ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 02/2016(ኢዜአ)፡- ብሔራዊ ተኃድሶ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሲቨል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ሂደት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ።

ሥምምነቱን የብሔራዊ ተኃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ሃና ወልደገብርኤል ፈርመውታል። 

በሥምምነቱ  መሰረት ሁለቱ ተቋማት የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ ሲቪል ሕይወት ለመመለስ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ በጋራ ይሰራሉ ተብሏል።  

ተቋማቱ  ኃብት ማሰባሰብ፣ ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን፣ መረጃ በመለዋወጥና በአቅም ግንባታ ሥራዎች በትብብር እንደሚሰሩም ተገልጿል። 

የብሔራዊ ተኃድሶ ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሲቪል ህይወት መመለስና መልሶ ለማቋቋም መንግሥት ከሚያከናውነው ተግባራት ባሻገር የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል።


 

በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር የተለያዩ ተግባራትን በትብብር ለመሥራት ሲያደርግ የነበረውን ውይይት በማጠናቀቁ ወደ ሥራ ለመግባት ሥምምነቱ መፈረሙን ገልጸዋል።

በሥምምነቱ መሰረት፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለቀድሞ ተዋጊዎች የሚያስፈልጉ የሥነ-ልቦና፣ የፋይናንስና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን እንደሚያመቻቹም ገልፀዋል። 

ሥምምነቱ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋምና በመደገፍ በኩል ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣ የሚያስችሉ የጋራ እቅዶች ወጥተው ተግባራዊ እንደሚሆኑም ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ሃና ወልደገብርኤል፤ ሥምምነቱ የሲቪል ማኅበረሰቡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚጫወተውን ሚና ከፍ የሚያደርገው ነው ብለዋል።


 

የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋምና በመደገፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። 

    

 

  

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም