የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዘንድሮው በጀት ዓመት 51 ቢሊየን ብር ብድር ለመስጠት ማዘጋጀቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዘንድሮው በጀት ዓመት 51 ቢሊየን ብር ብድር ለመስጠት ማዘጋጀቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 02 / 2016(ኢዜአ)፡ - የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዘንድሮው በጀት ዓመት 51 ቢሊየን ብር ብድር ለመስጠት ማዘጋጀቱን ገለጸ፡፡
የባንኩ የኮርፖሬት ኢንዱስትሪ ፋይናንሲንግ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ መሀሪ ለኢዜአ እንደገለጹት ፤ ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ11 ግዙፍ ፕሮጀክቶች 23 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ብድር ሰጥቷል ።
በዘንድሮው ዓመት ደግሞ 51 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ ከዚሁ ውስጥ 31 ነጥብ 4 ቢሊዮኑ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት በባንኩ ላይ የተከናወነው የሪፎርም ስራ ባንኩ የተሻለ የፋይናንስ አቅም እንዲፈጥር ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አኳያ አሁን ላይ ባንኩ አጠቃላይ የማበደር አቅም 200 ቢሊዮን ብር መድረሱን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ባንኩ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለኢንዱስትሪዎች የብድር ገንዘብ የማቅረብና ብድር የመሰብሰብ አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደገ ሲሆን የተበላሹ የብድር ምጣኔዎችን መቀነስ መቻሉንም አውስተዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት ለአንድ ደንበኛ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በብድር የመስጠት አቅም እንዳልነበረው አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለአንድ ተበዳሪ እስከ 10 ቢሊዮን ብር የመስጠት አቅም ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
ባንኩ በተጠናቀቀው የ2015 ዓም በጀት ዓመት 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ለኢንደስትሪ ዘርፍ የሚያቀርበውን የገንዘብ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ መምጣቱንም አንስተዋል።
የባንኩ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንሲንግ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አስፋው አበራ በበኩላቸው ፤ባለፉት ሶስት ዓመታት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ከመደገፍ አኳያ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ አቅርቦት በወቅቱ እንዲያገኙም ከማድረግ አንፃር የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቁመዋል ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በሊዝ ፋይናንስ ዘርፍ የነበረው የብድር አመላለስ ሁኔታ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠውን ብድር ከአንድ አመት በላይ ተቋርጦ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ችግሩን መቅረፍ በመቻሉ ኢንተርፕራይዞቹን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ባንኩ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለኢንደስትሪ ዘርፉ 49 ነጥብ5 ቢሊዮን ብርድ መስጠቱም ተገልጿል፡፡