ቀጥታ፡

ሁሉንም ተደራሽ ላደረገ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ ትኩረት ተሰጥቷል - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

ቢሾፍቱ፤ ጥቅምት 02/2016(ኢዜአ)፡- ለአደጋ ስጋት ተጋላጭ ያልሆነ ማህበረሰብና ሀገር ለመገንባት ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል ሲል የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለፀ።

የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ በመከበር ላይ ይገኛል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በዚሁ ጊዜ "ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያስከትሉት ጉዳቶች የልማትና የዕድገት አቅጣጫዎችን በአግባቡ እንድንፈትሽ አድርጎናል" ብለዋል።

በተለይም በቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ስራዎች፣ በአደጋ ጊዜ ምላሽና በድህረ አደጋ ስራዎች ዙሪያ ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ ቅንጅታዊ ርብርብ ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ላይ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም መቻሏን ገልጸው፤ ለአደጋ ስጋት ተጋላጭ ያልሆነ ማህበረሰብና ሀገር ለመገንባት ውስጣዊ አቅማችንን መሰረት ያደረገ የተቀናጀ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ ትኩረት አግኝቷል ብለዋል።

በዚህም ከቅድመ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ድህረ አደጋ የአደጋ ስጋት አመራር ምዕራፎች ላይ በራስ አቅም ችግሮችን መፍታት የምንችልበትን ዘላቂነት ያለው አቅም መገንባት እየተቻለ መሆኑን ነው ያነሱት።

ማህበረሰቡ ከጠባቂነት በመውጣት የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶች እንዲጎለብቱና አሰራሮቹ ተቋማዊ መልክ እንዲኖራቸው መስራት አለብን ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በዚህም ዘላቂ አቅም መገንባት ይቻላል ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ተወካይ ወይዘሮ ኤልዳና ሱሌይማን በበኩላቸው በክልሉ የህዝቡ ነባር የመረዳዳት እሴት ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው በማስቻልና የራስን አቅም በመጠቀም የአደጋ ስጋት መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ 10 ዞኖች የተከሰተው ድርቅ በርካታ ሀብት፣ እህልና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ችግሮቹን በውስጣዊ አቅም መቋቋም የተቻለበትን እንደ አብነት አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም