ቀጥታ፡

ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2016 (ኢዜአ)፡- ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ ፡፡

ስምምነቱን የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽነሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ሀና ወልደ ገብርኤል ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ  መሰረት ሁለቱ ተቋማት የቀድሞ  ተዋጊዎችን መልሶ ማቋቋምና ወደ ሲቪል ህይወት ለመመለስ  በጋራ ይሰራሉ፡፡ 

ተቋማቱ ሀብት ማሰባሰብ፣ ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን፣ መረጃ በመለዋወጥ እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ነው የተስማሙት።

ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የቀድሞ ተወጊዎችን ወደ ቀደመ ህይወታቸው የመመለስ ስራው የሁሉንም አካላት ትብብር ይፈልጋል።

በዚህ ረገድ ዛሬ የተደረገው ስምምነት ትልቅ ጅማሬ ነው ያሉት አምባሳደሩ በተለያዩ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

ስምምነቱ ተግባራዊ ሆኖ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣም በቁርጠኝነት መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ሀና ወልደ ገብርኤል በበኩላቸው የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ቀድሞ ህይወታቸው የመመለስ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ሚና ይወጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም