ቀጥታ፡

የልብ ህክምና አገልግሎትን በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የማስፋት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው - ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦የልብ ህክምና አገልግሎትን ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የማስፋት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

የዓለም ጤና ደርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በተለያዩ ምክንያቶች ለልብ ህመም የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል።

በልብ ህመም ሳቢያ በየዓመቱ በአማካይ 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች ለሞት እየተዳረጉ መሆኑንም ይጠቁማል።

በመሆኑም የልብ ጤንነትን ለመጠበቅ በተለይም ትንባሆ አለማጨስና በአመጋገብ የጨው መጠንን መቀነስ እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በተለይም አትክልትና ፍራፍሬን መመገብ ማዘውተርና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራትም አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የዓለም የልብ ቀን "ስለልብዎ ይወቁ ልብዎን ይንከባከቡ" በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ተከብሯል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ፈላጊዎች ቁጥር እየተሰጠ ካለው አገልግሎት አንፃር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የልብ ህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የልብ ህክምና አገልግሎትን በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የማስፋት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የልብ ማህበር ፕሬዝዳንት እንዳለ ገብሬ፤ የአለም ስጋት የሆነውን የልብ በሽታ ለማከም ቅንጅታዊ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም የህክምና ፈላጊዎችና አገልግሎቱ የተመጣጠነ አለመሆኑን ጠቅሰው የልብ ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

መንግስት ህክምናውን ለማስፋት የሚያደርገውን ጥረት የግሉ ዘርፍም አጋዥ በመሆን ለስኬቱ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በመርሃ ግብሩ የልብ ህሙማን ማህበርና የኢትዮ ኢስታቡል ጀነራል ሆስፒታል ለ300 ህጻናት ነጻ የልብ ቆዶ ህክምና ለመሥጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም