በመስከረም ወር የተከበሩ በዓላትን ለማወክ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም ህዝቡ በፍቅርና በሰላም አክብሯቸዋል- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በመስከረም ወር የተከበሩ በዓላትን ለማወክ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም ህዝቡ በፍቅርና በሰላም አክብሯቸዋል- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦በመስከረም ወር የተከበሩ በዓላትን ለማወክ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም ህዝቡ በፍቅርና በሰላም አንድነቱን አጽንቶ አክብሯቸዋል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ የበዓላቱ በሰላም መከበር የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና ሰላም ለመረበሽ ለሚሰሩት አካላት የኢትዮጵያ ሕዝብ የምንጊዜም ፍላጎት ሰላምና አንድነት መሆኑን ማሳየት ችሏል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ሕዝባዊ በዓላት ለሀገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት!
በመስከረም ወር የተከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ኹሉ እሴታቸውን ጠብቀው፣ ሀገራዊ አንድነትን አንፀባርቀውና ሰላምን ሰብከው ተጠናቅቀዋል፡፡
የመስቀል በዓል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከበሩት ጊፋታ፣ ያሆዴ፣ ዮ ማስቃላ፣ የቤኔ ሻዴዬ ባሮ፣ ቶኪ በአ፣ እና ሌሎችም የዘመን መለወጫ በዓላት በደማቅ ሁኔታ ተከብረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተከበረው ሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀርሰዲ በዓልም እጅግ ውብ በኾነ ባህላዊ መንገድ ተከብሮ በሰላም ተጠናቅቋል፡፡
የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓለም ሌላው በመስከረም ወር የተከበረ ታላቅ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓል ነው፡፡
እነዚህ በዓላት እንደወትሮው ሁሉ እፁብ ድንቅ በሆኑ ባህላዊ አልባሳት፣ ዝማሬዎች፣ ምግቦች እና ሁነቶች ደምቀው መከበራቸው ብቻ ሳይሆን ለሀገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት ተጨማሪ ኃይል ሆነው መጠናቀቃቸውም ያለው ሀገራዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
በእነዚህ በዓላት ላይ በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች በነቂስ ወጥቶ ታድሟል፡፡
የውጭ ቱሪስቶችም በበዓላቱ ላይ በብዛት ተሳትፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላት እምቅ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የቱሪስት መስህብም ጎልቶ ታይቷል፡፡
በበዓላቱ ላይ የተሳተፉት ታዳሚዎችም በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ላይ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠሩ የንግድ ልውውጦችን አከናውነዋል፡፡
በዓላቱን ለማድመቅ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብዓቶች፣ የትራንስፖርት ክፍያዎች፣ የምግብና የመጠጥ ሽያጮች፣ የፋሽንና ዲዛይን ሁነቶች፣ ኮንፈረንሶች፣ የአደባባይ ግብይቶች ወዘተ በበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ሲከናወኑ የነበሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡
በበዓላቱ ላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ሥፍራ በብዙ ቁጥር በመገኘት ሀገራዊ አንድነቱን አሳይቷል፤ ፍቅር ተለዋውጧል፣ ፈጣሪውን በአንድነት አመስግኗል፣ ባህልና ማንነቱን በጋራ ገልጧል፤ በፍቅር ተጎራርሶ ከልብ ተመራርቋል፤ በሕብረት ዘምሮ በአብሮነት ስሜት ጨፍሯል፡፡
ከመኖሪያ ቀያቸው ርቀው ሄደው በዓላቱን ያከበሩ ሰዎችም በታላቅ የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት በሁሉም አካባቢዎች በክብር ተስተናግደዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሀገራዊ የአብሮነት ስሜትን ያጠናከረ ታላቅ ክስተት ነበር፡፡
በሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ በአራቱም አቅጣጫ በተመሳሳይ ወቅት አንድነቱን ሲያፀና እና እርስ በርሱ በአብሮነት ሲተሳሰር ያለ አንዳች ኮሽታ በፍፁም ሰላማዊ መንገድ መሆኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰላም ውጭ ምንም አጀንዳ እንደሌለው ዳግም በተግባር የታየበት ነው፡፡
መንግሥት እና ሕዝብ ለዘላቂ ሰላም በትብብር እያከናወኑት ያለው ተግባር ፍሬ ማፍራቱንም በእነዚህ በዓላት ላይ በግልፅ ተመስክሯል፡፡
በተለያዩ አካላት በዓላቱ እንዲታወኩ ከፍተኛ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም፤ ሰሚ ጆሮ አጥተው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቅርና በሰላም አንድነቱን አፅንቶ በዓላቱን በሰላም አክብሯል፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና ሰላም ለመረበሽ ለሚሰሩት አካላትም የኢትዮጵያ ሕዝብ የምንግዜም ፍላጎት ሰላምና አንድነት መሆኑን አስተምሯል።
በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ርብርብ ያደረጉ የፀጥታ አካላት፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስተዳደር መዋቅሮችና በተለይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእጅጉ ሊመሰገን ይገባዋል።
በቀጣይ በሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላትም ሆነ በዕለታዊ መደበኛ እንቅስቃሴዎች የጀመሩትን ተናብቦ ለሰላም ዘብ የመሆን አቋም አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡