በሚቀጥሉት አስር ቀናት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር ይችላል- የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016 (ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋና ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛው በደቡብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ገጽታ ይኖራቸዋል።

ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋና ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር አንደሚችልም አመላክቷል።

በመካከለኛው፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁሟል።

ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ሁሉም የአርሲ፣ የባሌና የጉጂ ዞኖች፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌና የቦረና ዞን ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖራቸው ይችላል።

ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፡ መካከለኛው የሰሜንና የምዕራብ ጎንደር፣ የባህር ዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞንም እንዲሁ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ በሁሉም የሶማሌ ክልል ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል።

የጋምቤላ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ጎንደር፣ የሰሜን ወሎ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች፣ በትግራይ፣ ሐረሪ እና ድሬዳዋ በአንዳንድ ሥፍራዎቻቸው ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው እርጥበት ዘግይተው ለተዘሩና የእድገት ጊዜያቸውን ላልጨረሱ የመኸር ሰብሎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑንም አመላክቷል። 

ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት እና ጥምር ግብርና ለሚያካሂዱ ለደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍሎች ቀደም ብሎ የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ጠቁሟል፡፡ 

እርጥበቱ ለአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለአረንጓዴ እፅዋት ልምላሜ መሻሻልና የውሃ አቅርቦት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ተጠቁሟል። 

ውሃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውሃ ለመሰብሰብና ለማከማቸት መልካም አጋጣሚ ስለሚያገኙ ይህንኑ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርጉም በመግለጫው ተመላክቷል።

በሌላም በኩል በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ተገምቷል።

በመሆኑም ከወዲሁ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በማንሳት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲል ኢንስቲትዩቱ አስገንዝቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም