ቀጥታ፡

በቀጣዮቹ አስር አመታት 80 በመቶ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ታቅዷል-የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016 (ኢዜአ)፦ በቀጣዮቹ አስር አመታት 80 በመቶ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት መታቀዱን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የቀረቡበትና ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆየው 17 ኛው "ኢትዮ-ኮን" ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል ተከፍቷል። 

በኤግዚቢሽኑ የአገር ውስጥ እና የውጭ አለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወንድሙ ሴታ፤ ኤግዚቢሽኑን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ዘርፉ ለሀገራዊ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለአገራዊ የምርት እድገት /GDP/ አሁን ላይ የ470 ቢልዮን ብር አስተዋጽኦ እያበረከተ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ከግብርና ዘርፍ በመቀጠል ከፍተኛ የስራ እድል የሚፈጠርበት መስክ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም 17 ኛው "ኢትዮ-ኮን" ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የቀረቡበት ሁሉም ሊጎበኘው የሚገባ ሁነት መሆኑን ጠቁመዋል።

የፖሊሲ ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ ሚኒስቴሩ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አስታውሰው ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ በበቂ ሁኔታ በአገር ውስጥ መኖራቸውን ገልጸው ወደ ግብዓትነት ለመለወጥ ውስንነቶች መኖራቸውን አመላክተዋል።

ከኮንስትራክሽን ግብዓት 65 በመቶ የሚሆነው ከውጭ የሚገባ በመሆኑ አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣዮቹ አስር አመታት ከዋና ዋና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች 80 በመቶ የሚሆነውን በአገር ውስጥ ለማምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ግርማ ሀብተማርያም፤ ዘርፉ በግብዓት አቅርቦት የዋጋ ንረት እየተፈተነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግብይት ስርዓቱ ያልተስተካከለ መሆንና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችም ሌላኛው ፈተና መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የዘርፉን ችግሮች በጋራ መፍታትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም