ቀጥታ፡

የሀገሪቱን የማር ምርት ለማሳደግ ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ጋር የማቀናጀት ተግባር እየተከናወነ ነው-  የግብርና ሚኒስቴር 

ቦንጋ ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦ የሀገሪቱን የማር ምርት መጠን ለማሳደግ አቅም ያላቸውን አካባቢዎች በመለየት ተግባሩን ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ጋር የማቀናጀት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

አገሪቱ በአመት ከ500 ሺህ ቶን በላይ ማር የማምረት አቅም ቢኖራትም እየተመረተ ያለው ግን እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ምርቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ሚኒስቴሩ ገልጿል። 

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ የንብና ሀር ልማት ዴስክ ሀላፊ አቶ አዘዘ አያሌ ለኢዜአ እንዳሉት  እንደ ሀገር በዘርፉ ከፍተኛ አቅም ቢኖርም በዓመት እየተመረተ ያለው ግን በተለያዩ ምክንያቶች ዝቅተኛ ነው።


 

የንብ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው ከገበያው ጋር ለማስተሳሰር የምርት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ስለሆነም ለማር ምርት ተስማሚ የሆኑና ከፍተኛ አቅም ያላቸውን አካባቢዎች በመለየት ተግባሩን ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ጋር በማስተሳሰር ምርቱን የማሳደግ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል። 

ለዚህም የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከጀመረ ወዲህ የማር ማምረት ሁኔታ መነቃቃት እያሳየ መምጣቱን ጠቁመው ይህን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል። 

እንደ አገር ከ2 ሚሊዮን በላይ አናቢዎች እንዳሉ ጠቁመው ዘመናዊ የአመራረት ዘዴ ያለመከተል እና የግንዛቤ እጥረት አገሪቱ ከምርቱ በተገቢው ላለመጠቀሟ እንደ ዋነኛ ችግር አንስተዋል። 


 

በሀገሪቱ ከሚመረተው የማር ምርትና የንብ ሀብት ውስጥ 39 በመቶው የሚገኘው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እንደሆነ ጠቁመው በአውሮፓ ገበያ እጅግ ተፈላጊ የሆነው የ"ገተሜ ማር" በዚሁ አካባቢ የሚገኝ እንደሆነም አብራርተዋል።

ክልሉ በዘርፉ ያለውን አቅም ለመጠቀም  በልዩ ትኩረት ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው ዘርፉ ከተለያዩ የግብርና ስራዎች ጋር ተቀናጅቶ ውጤት ማስገኘት የሚችል በመሆኑ ዜጎች በዘርፉ ለመሰማራት ትኩረት እንዲያደርጉም ጠቁመዋል። 

የካፋ ዞን ግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ፅህፈት ቤት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ አረጋ በዞኑ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ  በ2015 በጀት ዓመት ከ19 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች ማር ይመረታል ያሉት የሸካ ዞን ግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ አዝመራ ፎአቶሸኖ በበኩላቸው በአብዛኛው በባህላዊ ዘዴ የሚመረት በመሆኑ የተፈለገው ጥቅም እንደማይሰጥ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ መንግስት በሰጠው ትኩረት አርሶ አደሩ ከባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ አመራረት እየተሸጋገረ በመምጣቱ ምርቱም እያደገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በደቡብ ምዕራብ ክልል የማር ምርት በሰፊው ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል  የካፋ እና የሸካ ዞኖች በዋነኝነት እንደሚጠቀሱም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም