ለስደተኞችና ተቀባይ ሀገራት የሚደረግ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጠየቀች - ኢዜአ አማርኛ
ለስደተኞችና ተቀባይ ሀገራት የሚደረግ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጠየቀች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲና አጋሮቹ ጫና እና ኃላፊነትን በመጋራት መርህ ለስደተኞች እና ተቀባይ ሀገራት ተጨባጭ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበች።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን 74ኛው የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ በስዊዘርላንድ - ጄኔቫ እየተካሄደ ነው።
በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በመድረኩ እየተሳተፈ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የስደተኞች ጥበቃ እና ራስን መቻል ላይ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችን አስመልክቶ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን ዋና ዳይሬክተሯ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስተናገድ ከባድ ኃላፊነት እየተወጣች መሆኗን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በቀጠናው ባለው ግጭት ወደ ሀገሪቱ እየተመሙ ካሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ሁኔታ መስመር ለማስያዝ የተቀናጀ የቀውስ ምላሽ ያሻል ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ እና አጋሮች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ በቀጣይም ጫና እና ኃላፊነትን በመጋራት መርህ ለስደተኞች እና ተቀባይ ሀገራት ተጨባጭ አጋርነት እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።