ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

በሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ ትኩረት ያደረገው "የእንቆጳ" ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው መክፈቻ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ያላትን አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በዲጂታል ኢኮኖሚው ረገድ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ድርጅቶችና ስራ ፈጣሪዎች በጉባኤው መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ከጉባኤው በተጓዳኝ የተዘጋጀው አውደ ርእይ አላማም በዲጂታል የሥራ ፈጠራ ያለውን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅና የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።


 

ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከመጡ ኢንቨስተሮችና ባለሃብቶች ጋር ትስስር የሚፈጥሩበት ስለመሆኑም አንስተዋል።

በጉባኤው ከ26 ሀገራት የተውጣጡ ስራ ፈጣሪዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትና የኢትዮጵያ ልምድና ተሞክሮ የሚጋሩበት መሆኑን ገልጸዋል።

በኤግዚብሽኑ ላይ የተሳተፉ ሥራ ፈጣሪዎችና የቴክኖሎጂ አልሚዎች ጉባኤው በርካታ ልምድና ተሞክሮ የተጋራንበት ነው ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው "የእንቆጳ" ጉባኤ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ቴክኖሎጂ አልሚዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ጀማሪ የንግድ ሥራ ባለሙያዎች እንዲሁም የትምህርትና የፋይናንስ ተቋማት  እየተሳተፋ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም