በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉትን ለመመለስና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መግባባት ላይ ተደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉትን ለመመለስና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መግባባት ላይ ተደረሰ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉትን ለመመለስና ችግሮችን በዘላቂነት በጋራ ለመፍታት መግባባት ላይ መደረሱን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ።
ጉባኤው ከስልጤ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር በቅበት ከተማ የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የምክክር መድረኩን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ ጉባኤው የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ኮሚቴ አዋቅሮ ሲሰራ ቆይቷል።
በኮሚቴው ጥናት መሰረት የነበሩ ችግሮች ተለይተው ከህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ምክክር እንደተደረገባቸውም ነው ያስረዱት።
ተፈናቃይ ወገኖችን ጨምሮ ከሁሉም ማህበረሰብ ክፍል ተወካዮችና ከመንግሥት መዋቅር አካላት ጋር ለሁለት ቀናት ውይይት መካሄዱንም ገልፀዋል።
በዛሬው የምክክር መድረክም የተፈጠረውን ችግር ፈትቶ ወደነበረበት ሰላማዊና የአብሮነት ኑሮ ለመመለስ ሁሉም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ነው ያሉት።
ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በጋራ ለመፍታት ኮሜቴ መቋቋሙን ገልፀው፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ከአንድ ሳምንት በኋላ እንዲመለሱ የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የግጭት መባባስ መንስኤ የሆኑ ጥፋተኞች፣ ዜጎችን ያፈናቀሉና ንብረት ያወደሙ ሰዎች በሕግ ተጠያቂ ይደረጋሉ ብለዋል።
የወደሙ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በኮሚቴው አስተባባሪነት በጋራ እንደሚገነቡም ጠቁመዋል።
የቤቶችን ግንባታም በአንድ ሳምንት ጊዜ አጠናቅቆ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ጉባኤው በቀጣይም ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ አተኩሮ ይሰራል ነው ያሉት።
የጉባኤው ስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላትም ተጎጂ ቤተሰቦችን የማፅናናት፣ የተጎዱትን እና ተፈናቃዮችን የመጠየቅ ተግባራት ማከናወናቸውንም ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ አክለው ገልፀዋል።