ቀጥታ፡

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የቀረቡበት 17 ኛው "ኢትዮ-ኮን" ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ተከፈተ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የቀረቡበት 17 ኛው "ኢትዮ-ኮን" ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል ተከፈተ።

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወንድሙ ሴታ፤ ኤግዚቢሽኑን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ዘርፉ ለሀገራዊ ምርት እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል።

በዚሀም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለአገራዊ የምርት እድገት /GDP/ አሁን ላይ የ470 ቢልዮን ብር አስተዋጽኦ እያበረከተ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ከግብርና ዘርፍ በመቀጠል ከፍተኛ የስራ እድል የሚፈጠርበት መስክ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም 17 ኛው "ኢትዮ-ኮን" ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የቀረቡበት ሁሉም ሊጎበኘው የሚገባ ሁነት መሆኑን ጠቁመዋል።

የፖሊሲ ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ ሚኒስቴሩ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አስታውሰው ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዝደንት ኢንጅነር ግርማ ሀብተማርያም በበኩላቸው፤ ዘርፉ በግብአት አቅርቦት የዋጋ ንረት እየተፈተነ መሆኑን ጠቅስዋል።

የግብይት ስርአቱ ያልተስተካከለ መሆንና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችም ሌላኛው ፈተና መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የዘርፉን ችግሮች በጋራ መፍታትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንም በስፋት መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

የተከፈተው ኤግዚቢሽንም በዘርፉ እያደገ የመጣውን ቴክኖሎጂ ለማወቅና ልምድ ለመቀመር የሚጠቅም መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም