ቀጥታ፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡት መግለጫ ተቀባይነት የለውም - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጡት መግለጫ ኃላፊነት የጎደለው በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ልዩ አማካሪዋ አሊስ ዋይሪሙ ያወጡት መግለጫ ኃላፊነት የጎደለውና መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የማያሳይ ነው ብሏል።

የልዩ አማካሪዋ መግለጫ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጣውን የተሳሳተ ሪፖርት መሰረት ያደረገ መሆኑንም ጠቅሷል።

ሪፖርቱ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበና አስተማማማኝ ካልሆነ የመረጃ ምንጭ የተሰበሰበ መሆኑን የገለጸው መግለጫው ይህም የሪፖርቱን ትክክለኛነትና ተዓማኒነት ውድቅ የሚያደርግ ነው ብሏል።

በመሆኑም የዘር ማጥፋት ወንጀልን የመከላከል ትልቅ ኃላፊነት የተሰጣቸው ልዩ አማካሪዋ በኢትዮጵያ ላይ ይህንን ያልተረጋገጠ ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨታቸው ኢትዮጵያን እንዳሳዘናት መግለጫው አመላክቷል።

የአፍሪካ ኅብረት የክትትል፣ አስከባሪና አረጋጋጭ ኮሚቴም ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ የመበተንና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ በአግባቡ እየተከታተለ መሆኑ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ሥምምነቱ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ እንዲሆን ቁርጠኛ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ ፍትህና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም እንዲሁ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ውይይቶችን በማድረግ ቁርሾዎችን በመሻር የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የሰላም ሥምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆንና በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም ድጋፉን ያጠናክራል ብላ እንደምትጠብቅ ተገልጿል።

በመሆኑም ልዩ አማካሪዋ የሰላም ሥምምነቱን በተመለከተ “ከዓመት በፊት የተደረሰው የሰላም ሥምምት ውጤት አላመጣም” በማለት ያስቀመጡት የተዛባ ግምገማ ትክክለኛ ያልሆነ በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው መግለጫው አመላክቷል።

የልዩ አማካሪዋ መግለጫ በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን ከሚደረገው ጥረት ጋር የሚቃረን በመሆኑ ሊያስተባብሉ ይገባል ብሏል መግለጫው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም