የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች ፍትሐዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች ፍትሐዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ኤሌክትሪክን በፍትሐዊነት ለማዳረስ በትኩረት እንዲሰራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪፊኬሽን መርሐ-ግብር ማስፈፀሚያ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር የተገኘውን 250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ስምምነት አፅድቋል።
የምክር ቤቱ አባላት በብድር ስምምነቱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ጥያቄ አንስተው ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያም ተሰጥቷል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዳረስ ላይ ዜጎች ቅሬታ የሚያነሱ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ባገኘው የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር በሁሉም አካባቢዎች ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንዳለበት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ዳይሬክተር ለምለም ምስጋናው እንደጠቀሱት፤ ቀደም ሲል ከዓለም ባንክ በተገኘ 375 ሚሊዮን ዶላር ብድር 941 ሺህ አባወራዎችን ከዋናው የሃይል መረብ ጋር በማስተሳሰር የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ከዚህ ባለፈ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎችንም ከዋናው መስመር ውጪ በተለያዩ የሃይል አማራጮች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ መደረጉን አንስተዋል።
ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር በተገኘውና ዛሬ በጸደቀው የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድርም ኤሌክትሪክ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ከ800 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አንስተዋል።
የኤሌክትሪክ መስመር ሊደርስ በሚችልባቸው ቦታዎች አዳዲስ መስመሮችን መዘርጋትና ነባሩን መስመር በማሻሻል የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እንደሚሰራም ነው የገለጹት።
ከዚህ ውጪ የተቋሙን እንዲሁም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መርሐ-ግብሩን የማስፈጸም አቅማቸውን ለማጎልበት ይረዳል ብለዋል።
ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው ሌሎች አራት የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን አፅድቋል።
ከእነዚህም መካከል መንግስት ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር ለሰው ሃብት ልማት ማስፈጸሚያ የተዋዋለው የ50 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አንዱ ነው።
ስምምነቱ በሁሉም ክልሎች ጤና፣ ትምህርት፣ ግብርናና ውሃ ላይ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችል መሆኑን የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል የቡና እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክትን ለማሻሻል፣ ለተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ እንዲሁም ለተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተፈረሙ የብድር ስምምነቶችንም አጽድቋል።
የብድር ስምምነቶቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉና ዜጎችን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲውሉ በየደረጃው ያሉ አመራሮች በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ምክር ቤቱ አሳስቧል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን ለሰው ሃብት ልማት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።