ኢንስቲትዩቱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ወዳልተለመደባቸው አካባቢዎች ለማስፋት የምርምርና የሰርቶ ማሳያ ስራዎች እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ወዳልተለመደባቸው አካባቢዎች ለማስፋት የምርምርና የሰርቶ ማሳያ ስራዎች እያከናወነ ነው
ጅማ ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ወዳልተለመደባቸው አካባቢዎች ለማስፋት የምርምርና የሰርቶ ማሳያ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
ባለፉት አራት ዓመታት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዘርፍ በተሰራው ስራ ልማቱ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች እየተለመደ ይገኛል።
በተያዘው ዓመት ብቻ በመላ አገሪቷ 3 ሚሊዮን ሄክታር በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 117 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል።
የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና የውሃ መሳቢያ ሞተር የመሳሰሉ ግብአቶችና የቴክኖሎጂዎች ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
የተያዘውን ግብ ለማሳካት ደግሞ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከዚህ ቀደም ወዳልተለመደባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች ለማስፋት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በስንዴ ልማት ላይ ብቻ ያተኮረ ማዕከል አቋቁሞ ምርምር ሲያካሄድ ቆይቷል።
በኢንስቲትዩቱ የስንዴ ምርምር ማዕከል የበጋ መስኖ ስንዴን የሚያርስበት የሰርቶ ማሳያ እርሻ ማሳዎች እንዳሉትም አስታውሰዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ደግሞ የምርምር ተቋሙ የጀመረው የመስኖ ስንዴ ልማት በመንግስት ትኩረት አግኝቶ በስፋት እንዲተገበር በመደረጉ ኢንስቲትዩቱም ይህን ጥረት እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
በኦሞ፣ በሸበሌና በአዋሽ ሸለቆዎች የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም ውጤታማ እየሆነ ምጣቱን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱም ተስፋ የታየበትን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከዚህ በፊት ወዳልተለመደባቸው አካባቢዎች ለማስፋት የምርምርና የሰርቶ ማሳያ ስራዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም አርሶ አደሮችና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች በኢንስቲትዩቱ የምርምር ማእከላት የቅርብ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመስኖ ስንዴ ልማት አስተባባሪ ዶክተር ዳንኤል ሙለታ በበኩላቸው የምርምር ኢንስቲትዩቱ የስንዴ አመራረት መመሪያ ማዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰራችው የመስኖ ስንዴ ልማት 'ኢኒሼቲቭ' ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ከመተካት አልፋ ወደ ውጪ መላክ መጀመሯም ትልቅ የልማት እመርታ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱም ይሄ ጅምር የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው የመስኖ ስንዴ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ምርታማነታቸው እንዲያድግ እንዲሁም ወደ አዳዲስ አካባቢዎች የማለማመድ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግርዋል።
በተለይም የስንዴን ምርታማነት ለመጨመር በመስኖ ባለሙያዎች በመታገዝና በሚሰጡት ምክረ ሀሳብ መሰረት ለማምረት መሞከር ያስፈልጋል ብለዋል።