የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት ህዝባዊ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት ህዝባዊ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ በተፈጠረ አለመግባባት የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ህዝባዊ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ የትኛውም ሃይማኖት መከባበርና መዋደድ እንጂ ጥላቻና ግጭትን የሚሰብክ አስተምህሮ እንደሌለው ተናግረዋል።
በመሆኑም አንዳንድ አካላት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት በሃይማኖት ሽፋን የሚቀሰቅሱት ግጭት ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ የሚጻረር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በቅበት ከተማ በተፈጠረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መጎብኘቱን ጠቅሰው ችግሩ በሰላም እንዲፈታ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የስልጤ ዞን ህዝብ ለዘመናት የቀጠለው አብሮነትና ትስስሩ እንዳይሻክር የግጭት ጠንሳሾችን ሴራ በአንድነት ማክሸፍ አለበት ነው ያሉት
የጉባዔው ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ሸኽ አብዱል አህመድ በበኩላቸው፣ ጉባኤው የተራራቁትን ለማቀራረብ፣ ለማስታረቅና አብሮነትን ለማጠናከር ወደ ቅበት መምጣቱን ገልጸዋል።
የስልጤ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ከድር አብደላ በበኩላቸው መከሰት ያልነበረበት ግጭት ተከስቶ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰዋል።
ህዝባዊ ውይይቱ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የተፈጠረው ግጭት ሁሉንም ያሳዘነ መሆኑን ገልፀው፣ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ነው ያነሱት።
ለግጭቱ መንስኤ የሆኑ ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል።