ቀጥታ፡

መቱ ዩኒቨርሲቲ የስንዴና የጤፍ ምርጥ ዘር በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያባዛ ነው

መቱ ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦  መቱ ዩኒቨርሲቲ የተሻለ ዝሪያ ያላቸውን ስንዴና ጤፍ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በምርምር የማውጣትና የማባዛት ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በኢሉባቦርና ቡኖ በደሌ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያከናወነ የሚገኘው የምርምርና ማባዛት ስራ በ16 የስንዴና 20 የጤፍ ዝሪያዎች ላይ መሆኑንም ገልጿል።

የምርምር ስራው በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ መካሄዱ ደግሞ አርሶ አደሩን ከተለመደው አስተራረስ ዘዴ በማላቀቅ  ሰብልን በማፈራረቅ ምርታማ መሆን እንዲችሉ በቅርበት ለማሳየት የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮችና የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር በድሉ ተካ እንዳሉት በተለይ በዘመናዊ ግብርናና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ መስክ የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ወደ ኅብረተሰቡ ወርደው ተጨባጭ ውጤት ማሳየት እንዲችሉ እየተደረገ ነው።

በዚህም ውጤታማነታቸው በጥናት የተረጋገጠ የስንዴና የጤፍ ዝሪያዎችን ለአርሶ አደሮች ማቅረብ የሚያስችለውን የምርምር ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ምርምሩ በ16 ያህል የስንዴና 20 የጤፍ ዝሪያዎች ላይ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በምርምሩ ምርታማነታቸው የተሻለ፣ በሽታን መቋቋም የሚችሉና በአካባቢው አየር ይበልጥ ሊለሙ የሚችሉ ዝሪያዎች ተለይተው ሲወጡ የግብርና ሴክተሩ እነዚህን ዝሪያዎች ተቀብለው ለአርሶ አደሮች እንዲያቀርቡ ይደረጋል ብለዋል።  

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲዉ በምርምር ስራዎቹ  ለኢኮኖሚ ዕድገቱ መረጋገጥ ሊያግዙ የሚችሉ የምርምር ውጤቶችን በአገር ደረጃ ለማቅረብ ሀሳብ እንዳላቸው ገልፀዋል።

በመቱ ዩኒቨርሲቲ የበደሌ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የዕጽዋት ሳይንስ መምህርና የሰብል ዝሪያ ማሻሻያ ተመራማሪ መምህር ጋሩማ ሽፈራሁ በበኩላቸው ምርጥ ዘሮችን ለመለየት የሚያስችል የምርምር ስራ በ20  የጤፍ እና በ16 የስንዴ ዝርያዎች ላይ እያካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በምርምሩም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ውጤታማነታቸው  የተረጋገጡትን በግብርና ኤክስቴንሽን በኩል  ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ የሚደረግ ነው ብለዋል።

በስንዴ ዝሪያ ላይ ምርምር እያደረጉ ከሚገኙ የኮሌጁ ተመራማሪዎች መካከል መምህር ለገሱ ብርሼ ዴቢሳ እንዳሉት መንግስት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለመተካት የያዘውን አቅጣጫ ስኬታማ ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የድርሻውን በማበርከት ላይ ነው ብለዋል።

በዚህም ከተለያዩ የግብርና ምርምር ማዕከላት የተገኙ ምርጥ ዘሮችን በመውሰድ በኢሉባቦርና ቡኖ በደሌ ዞኖች ይበልጥ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ የስንዴ ዝሪያዎችን ለመለየት የሚያስችል ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።      

ዩኒቨርሲቲው በምርምር ስራው ግብርናውን ከማዘመን ባሻገር እንደ ሀገር የተያዙትን አቅጣጫዎች ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ የገለጸው ደግሞ የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ነው።

የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ በመቱ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በስንዴና ጤፍ ዝሪያዎች ላይ እየተካሄደ የሚገኘው የምርምር ስራ ምርታማነትን ለመጨመር ግብርናውን ለማዘመን የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በምርምሩ በአካባቢው ሊለሙና ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ ዝሪያዎች እንደሚገኙ የሚጠበቅ መሆኑን ያነሱት አቶ ቻላቸው፤  በዚህም የዞኑን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር መፍታት እንደሚቻል ተስፋ የተጣለበት መሆኑንም አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም