ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ስኬታማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ አከናውናለች-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወዳጅ በማብዛትና ጠላት በመቀነስ ስኬታማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ማከናወን መቻሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት፣ በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ወደ መደበኛ በመመለስ አጋር ማብዛት የሚል መሆኑን ጠቅሰው፤ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ የሚያስችል ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ዋና ግቡም ጠላትን በመቀነስ ወዳጅ ማብዛት መሆኑን የገለጹት አምባሳደር መለስ፤ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይናና መሰል ሀገራትና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር የነበረው የዲፕሎማሲ መስተጋብር ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተመዘገቡበት ነበር ብለዋል።

ለአብነትም ከአሜሪካ መንግስት ጋር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የልማት ትብብር፤ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በመከላከያና ጸጥታ ጉዳይ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ  በዲሞክራሲ፤ ሰብዓዊ መብትና መልካም አስተዳደር ብሎም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከ78ኛው የተመድ ስብሰባ ጎን ለጎን ከ30 በላይ የሀገር መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ሀላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ያደረገው የፋይናንስ ድጋፍም በሩብ ዓመቱ የተመዘገበው የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ክሮሽያ፣ ኮሎምቢያ እና መሰል ሀገሮች በኢትዮጵያ ኤምባሲያቸውን ለመክፈት ፍላጎታቸውን እያሳዩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም