ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ አንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2016(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ አንዲቀጥል ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሲያከናውናቸው የቆየውን ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ዛሬ ገለጻ አድርጓል።


 

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በገለጻቸው፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለምክክሩ መጀመር መሰረታዊና ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ መሆኑን አንስተዋል::

በዚህም አገራዊ ምክክሩ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል ከፌዴራል እስከ ክልሎች ከክልሎች አስከ ዞኖች እና ወረዳዎች በመድረስ ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ ዛሬ የተደረገው ገለጻ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት እገዛቸውን እንዲያጠናክሩ ያስችላል ነው ያሉት።


 

እስካሁን ባለው ሂደትም በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ በተከፈተ የትረስት ፈንድ ቋት ውስጥ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ10 ሚሊየን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቀጣይም ኮሚሽኑ ስለሚሰራቸው ተግባራት ተገንዝቦ ኮሚሽኑ የሚሰራቸው ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም