ቀጥታ፡

ማህበሩ ለሁለት ሆስፒታሎች የተለያዩ መድሃኒቶች ድጋፍ አደረገ

ጎንደር ፤ መስከረም 30/2016(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ  የተለያዩ ዓይነት መድሃኒቶችን ለጎንደር ዩንቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ለአይራ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ፡፡

በማህበሩ የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ እንደተናገሩት፤ የተደረገው ድጋፍ ሆስፒታሎቹ የሚሰጡትን የህክምና አገልግሎት ለማጠናከር የሚያስችል ነው፡፡


 

መድሃኒቶቹ ለቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚውሉና በደም ስር የሚሰጡ ግሉኮሶችን ጨምሮ በጸረ ተዋስያን የሚከሰቱ በሽታዎችን ለማከም የሚያስችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመድሃኒት ድጋፉ የተገኘው ከዓለም ጤና ድርጅት መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም በሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለሚገኙ የጤና ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ማህበሩ በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎችን እያቀረበ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ 

የጎንደር ዩንቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘባቸው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ድጋፉ የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትን ያቃልላል።

የኢትዮጵ ቀይ መስቀል ማህበር ለሆስፒታሉ ያደረገው ድጋፍ ታካሚዎች በመድሃኒት እጥረት የሚደርስባቸውን እንግልትና ሌሎች ችግሮች ለማቃለል የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአይራ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንዳርግ ወንዳለ፣ ድጋፉ ሆስፒታሉ ማቅረብ ያልቻላቸውን መድሃኒቶች በቀላሉ ለማግኘት እንዳስቻለው ገልጸዋል፡፡  

በቀን 150 ህሙማን ህክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ እንደሚመጡ ጠቁመው፤ ድጋፉ በተለይም ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን እገዛው ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም