ቡናን ከምርት አሰባሰብ እስከ ገበያ አቅርቦት ያለውን ሂደት በተሻለ መልኩ ለመከወን የዘርፉ ተዋንያን በትብብር ሊሰሩ ይገባል- የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
ቡናን ከምርት አሰባሰብ እስከ ገበያ አቅርቦት ያለውን ሂደት በተሻለ መልኩ ለመከወን የዘርፉ ተዋንያን በትብብር ሊሰሩ ይገባል- የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር
ዲላ ፤ መስከረም 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቡናን ከምርት አሰባሰብ እስከ ገበያ አቅርቦት ያለውን ሂደት የተሻለ ለማድረግ የዘርፉ ተዋንያን በትብብር መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ገለጸ።
ማህበሩ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በቡና ጥራት አጠባበቅና ግብይት ዙሪያ የምክክር መድረክ በዲላ ከተማ አካሂዷል።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሁሴን አንቦ በወቅቱ እንዳሉት የኢትዮጰያ ቡና ተፈላጊነቱን ይበልጥ ለማሳደግ የዘርፉን ተዋንያን ያሳተፈ ብሔራዊ ማህበር ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።
ከምርት እስከ ዓለም አቀፍ ግብይት በቡና ዝግጅት፣ በምርትና በእሴት ሰንሰለት የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ሀገሪቷ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ ማነቆ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዓለም ላይ ከ120 በላይ ሃገራት ቡና እንደሚያቀርቡ ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ቡና ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን በቡና ጥራት አጠባበቅና በግብይቱ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዚህም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ከማቅረብ ጀምሮ ምርት ለገበያ እስኪቀርብ አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ጨምሮ ሁሉም የዘርፉ ተዋንያን በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በቡና ልማት የዘርፉ ተዋንያን በመንግስት በሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ዙሪያ ገንዛቤ በማስጨበጥ የቡና ጥራትና ግብይትን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ተወካይ አቶ ጋንታ ጋምኣ ቡናን በቴክኖሎጂና በግብዓት አጠቃቀም በመደገፍ ምርታማነቱን በመጠንና በጥራት የማሻሻሉ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ታጠቅ ዶሪ በበኩላቸው በዞኑ ከ74 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በቡና መሸፈኑን ጠቅሰው በዚህም ከ123 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ቡናን እያለሙ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም በየአመቱ በአማካይ ከ22 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዞኑ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቡና ግብይትና ምርታማነት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዚህም በተያዘው ዓመት ከ25 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ግብ ተጥሎ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልሉ ቡና አቅራቢ፣ የነጋዴ ማህበራት እንዲሁም የዘርፉ የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡና አቅራቢዎች ማህበርም በይፋ ተመስርቷል።