በዚህ ዓመት 200 ሺህ የሚደርሱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል ታቅዷል- የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በዚህ ዓመት 200 ሺህ የሚደርሱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል ታቅዷል- የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2016(ኢዜአ)፦ በዚህ ዓመት 200 ሺህ የሚደርሱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል መታቀዱን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን መንግስትና ህወሃት የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ከተቋቋመ 10 ወራትን አስቆጥሯል።
በእነዚህ ወራትም የቀድሞ ተዋጊዎች ከሚገኙባቸው ክልሎች አመራሮችና የተሃድሶ ፕሮግራሙን በገንዘብ ከሚደግፉ አጋሮች ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ፤ የኮሚሽኑን የስራ እንቅስቃሴ በማስመልከት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከጥር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ኮሚሽኑ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል የሚያግዙ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት ስራዎችም ስለመከናወናቸው አስታውሰው በሀገሪቱ ስምንት ክልሎች በውጊያ ላይ ሲሳተፉ የነበሩ 371 ሺህ 971 የቀድሞ ተዋጊዎችን መለየቱን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም ከ150 ሺህ እስከ 200 ሺህ ያህሉን አስፈላጊውን የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል ብለዋል።
በጦርነት አውድ ውስጥ የቆየውን የተዋጊዎችን ስነ ልቦና ለሰላምና ምርታማነት ለማዘጋጀት አዕምሯዊ ዝግጅት፣ የፖለቲካ ግንዛቤና ማህበራዊ ተሃድሶ ለመስጠት የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ስራውን ለማከናወን የሚያግዘውን የሁለት ዓመት ፕሮግራምና ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ አስፈላጊውን ገንዘብ ለማግኘት ከዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የልማት አጋሮች ጋር ውይይት ማድረጉንም ተናግረዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎቹ ስልጠና የሚያገኙባቸው ማዕከላት ግንባታና የማሰልጠኛ ሰነዶች አለመጠናቀቃቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ እነዚህን ለማሳካት ርብርብ እያደረግን ነው ብለዋል።
ለአብነትም እያንዳንዳቸው 5 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን መያዝ የሚችሉ 5 ትላልቅ ማዕከላትን በ500 ሚሊዮን ብር መልሶ ለመገንባት ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ማዕከላቱም የማሰልጠኛ፣ የሰልጣኞች መኝታ፣ የህክምና፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የመመገቢያና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን ማሟላት የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል።
በተሃድሶ ፕሮግራሙ በተለያዩ ምዕራፎች ተዋጊዎቹን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል መታቀዱን ጠቅሰው፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሸኛቸው 50 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችም በፕሮግራሙ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
መንግስት ለተሃድሶ መርሐ ግብሩ መሳካት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የልማት አጋሮችም አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ቃል እየገቡ ነው ብለዋል።
በዚህም ከጥር ወር ጀምሮ ቃል የተገቡ ገንዘቦች ለኮሚሽኑ ገቢ እንደሚደረጉ ተስፋ አለን ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የሀገር ውስጥ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና ሌሎችም በልዩ ልዩ መንገድ የኮሚሽኑን ተልዕኮ ለመሳካት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ ታልሞ ህዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት መቋቋሙ ይታወቃል።
ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎች በሀገሪቱ የልማት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንዲሳተፉ ማስቻልም ዋና ተልዕኮው ነው።