በሀገሪቱ የሮዝመሪ ምርት እንዲስፋፋ ዝርያውን የማላመድና የማባዛት ተግባር እየተከናወነ ነው-ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ የሮዝመሪ ምርት እንዲስፋፋ ዝርያውን የማላመድና የማባዛት ተግባር እየተከናወነ ነው-ኢንስቲትዩቱ
ሀዋሳ ፤መስከረም 30/2016 (ኢዜአ)፦ በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣውን የሮዝመሪ ምርት ለማስፋፋት እንዲቻል ዝርያውን በተለያዩ ክልሎች የማላመድና የማባዛት ተግባር እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የወንዶገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ ሙሉቀን ፊሊጶስ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ በስምንት ዘርፎች የተለያዩ የምርምር ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።
በዋናነትም በመዓዛማና በመድሃኒት ዕፅዋቶች ላይ በማተኮር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዕፅዋቶቹ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቅሰው ልማቱን ለማሳለጥ እንዲቻል ማእከሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ዝርያዎችን የማላመድና የማባዛት ተግባር እያከናወነ መሆኑን አውስተዋል።
በተለይ በስልጤ ዞን በሰርቶ ማሳያ ተሞክሮ ከፍተኛ ውጤት ያስገኘውን የሮዝመሪ ዝርያ በኦሮሚያ፣ በሲዳማና በደቡብ ምዕራብ ክልሎች በሚገኙ የተቋማትና አርሶ አደሮች ማሳ ምርቱን የማባዛት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የሮዝመሪ ምርት በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ ማዕከሉ ወደ ዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ክልሎች መነሻ ዘር በማዘጋጀትና ስልጠና በመስጠት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በማዕከሉ አሁን ላይ ዝርያቸው በተለዩ ሶስት የሮዝመሪ ዓይነቶች ላይ በርካታ የምርምር ስራ መከናወኑን ገልጸው በቀጣይ ጥቅም ላይ ሲውሉ ልማቱን ለማስፋፋት ወሳኝ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በማዕከሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪና የምርምር ክፍሉ አስተባባሪ አቶ ዋሲሁን አለምነው በበኩላቸው የመዓዛማና የመድሃኒት እፅዋቶች ከሚያስገኙት ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አንጻር ትኩረት አልተሰጣቸውም ባይ ናቸው።
ሆኖም ማእከሉ የመዓዛማና የመድሃኒት ዕፅዋትን በሚፈለገው ልክ ለማባዛትና ለማላመድ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሲዳማ ክልል በሚገኙ በተመረጡ ትምህርት ቤቶችና ሞዴል አርሶ አደር ማሳ ላይ ምርቱን ለማባዛት ከ136 ሺህ በላይ መነሻ የሮዝመሪ ችግኞች በማከፋፈል ምርቱን የማባዛት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ከምርምር ማዕከሉ ጋር በመቀናጀት በመዓዛማና በመድሃኒት ዕፅዋት ላይ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ በሲዳማ ክልል ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማት ባለስልጣን የዘርፉ ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ምንዳዬ ምትኩ ናቸው።
በክልሉ ሮዝመሪን ጨምሮ ከስድስት የሚበልጡ የመዓዛማና የመድሃኒት ዕፅዋትን ለማባዛት በሶስት ወረዳዎች ላይ ሶስት ችግኝ ጣቢያዎች በማቋቋም 740 አርሶ አደሮች በማደራጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል።
በሸበዲኖ ወረዳ ቴላሞ ቀንጥሴ ትምህርት ቤት ውስጥ የወላጅ ኮሚቴ የሆኑት አርሶ አደር ቢሊሶ ኮረሳ በትምህርት ቤቱ ግቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ሮዝመሪን በማልማት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ከባለሙያዎች ባገኙት ድጋፍ የተሻለ ምርት ለማግኘት በመስራታቸው ጥሩ ውጤት እንደሚጠብቁ ገልጸው ምርቱን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በማስተዋወቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
የወንዶገነት ግብርና ምርምር ማዕከል 33 የዕፅዋት ዝርያዎችን ለተለያዩ ጥቅሞች የማዋል ሥራ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።