አገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ አገሪቱ ያላትን የዘርፉ ፀጋዎች ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያግዛል - የአውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ አገሪቱ ያላትን የዘርፉ ፀጋዎች ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያግዛል - የአውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2016(ኢዜአ)፦አገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ፀጋዎች ይበልጥ ለማስተዋወቅና የዘርፉን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዕድል እንደሚፈጥር ኢዜአ ያነጋገራቸው የአውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገር አቀፉን የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ-ርዕይ በትላንትናው እለት መርቀው ለእይታ ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎች፤ አውደ-ርዕዩ በየክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም እምቅ ኃብቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
በዚህም አገሪቱ በዘርፉ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ዕድል እንደሚሰጣት ነው ያብራሩት።
የአፋር ክልል ተሳታፊ ኖራ ጁሃር፤ አውደ-ርዕዩ በኢትዮጵያ ምን ያህል ኃብቶች እንዳሉ ያሳየ መሆኑን ጠቁሞ፤ በኢትዮጵያ ያሉ ውብ ባህሎችን አውቆ ለማሳወቅ የሚያግዝ መሆኑን ገልጿል።
የአማራ ክልል ተሳታፊ መልኬ በላይነህ፤ አውደ-ርዕዩ የአገሪቱን የተፈጥሮ ፀጋ በማስተዋወቅ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለመሳብ ዕድል እንደሚሰጥ አስገንዝቧል።
የኦሮሚያ ክልል ተሳታፊ ማኅደር ፍቃዱ፤ ያሉንን የቱሪዝም መዳረሻዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብላለች።
በየአካባቢው ስላሉን መስህቦች በቂ እውቀት ሊኖር እንደሚገባና አውደ-ርዕዩ ይህንን በመፍጠር በኩል ጉልህ አስተዋፅዖ አለው ነው ያለችው።
ሌላኛው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተሳታፊ አልበሽር አወድም፤ መድረኩ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚያገናኝ እንዲሁም ልምድ የሚለዋወጡበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ተሳታፊ ከማል ዘካሪያም አውደ-ርዕዩ ከየአካባቢው የተለያዩ ልምድ የሚቀመርበት መሆኑን ገልጿል።
የመጣበትንም ክልል እንዲሁም የሌሎችንም በመመልከትና በማሳወቅ የዘርፉን አቅም ለማሳደግ እንደሚያግዝም እንዲሁ።
እስካሁን ያልታወቁ በርካታ ቦታዎች በአውደ-ርዕዩ ለመመልከት መቻሉን የገለጸው ደግሞ የሐረሪ ክልል ተሳታፊው አብዱልናስር አብዱላሂ ነው።
የሲዳማዋ ተሳታፊ አልማዝ አንበርብር፤ መድረኩ ክልሎች ያላቸውን እምቅ የቱሪዝም ኃብት ለመላው ዓለም የሚያሳዩበት መሆኑን ገልፀዋል።
እንዲሁም ክልሎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ያላቸውን አቅም የሚያውቁበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ተሳታፊ ለምለም አሥራት፤ አውደ-ርዕዩ እርስ በርስ ያሉ አቅሞችን ለመረዳትና ትውውቁንም የሚያጠናክር መሆኑን ገልጻለች።
አውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያን በአንድ ማዕከል ያሳየ ነው ያለው ደግሞ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተገኘው ወንድሙ አባተ ነው።
ሁሉንም አካባቢዎች ተዘዋውሮ ለመመልከት አቅሙ ያልቻለ ሰው በዚህ አውደ-ርዕይ ሁሉንም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለመመልከት እንደሚችል ተናግሯል።