ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በቡና ተክል ከለማው መሬት 30 ሺህ 771 ሄክታሩ ምርት መስጠት ጀምሯል- የክልሉ ግብርና ቢሮ

ባህር ዳር፤  መስከረም 30 /2016 (ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልል በቡና ተክል ከለማው መሬት   30 ሺህ 771 ሄክታር ምርት መስጠት መጀመሩን  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ፤  የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን  በማላመድ የተሻሉትን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

በግብርና ቢሮው የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ጌታቸው አዲስ ፤ የክልሉን የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለዚህም ባለፉት ዓመታት በኩታ ገጠምና በመደበኛው በተካሄደ የቡና ልማት ከ38 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ማልማት እንደተቻለ አስረድተዋል።

የቡና ልማቱ በ19 ወረዳዎች በኩታ ገጠም አሰራር ታግዞ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተው፤  ምርቱ የሚሰበሰበውም በቡና ተክል ከለማውና ምርት መስጠት በጀመረው 30 ሺህ 771 ሄክታር መሬት ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።

 ከዚህም ወደ 153 ሺህ 855 ኩንታል እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን ብለዋል። 

ከሚሰበሰበው ምርት ውስጥም ከ5 ሺህ 800 ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በአማራ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየንና በአየሁ እርሻ ልማት ድርጅት አማካኝነት ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን  ገልጸዋል።

ለዚህም አምራች አርሶ አደሮች ምርቱን የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲሰበስቡ በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛና ክትትል ለማመቻቸት  ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  አመልክተዋል።

የአማራ ገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር  ዩኒየን ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማሬ ጌትነት እንዳሉት፤  ዩኒየኑ 24 መሰረታዊ ቡና አምራች ማህበራትን በመያዝ እየሰራ ይገኛል።


 

በተለይ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒየኑ የክልሉን የቡና ምርት በአለም ገበያ ለማስተዋወቅ ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት እየላከ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እየተመረተ ለገበያ እየቀረበ ያለው ቡና የተፈጥሮ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተያዘው ዓመት 2 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ወደ ውጭ ለመላክ መታቀዱን አስረድተዋል።

በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የወራሚት አትክልትና ፍራፍሬ ንዑስ ማዕከል የቡና ተመራማሪ አቶ መለሰ ዋለ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣትና በማላመድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።


 

ከጅማ ምርምር ማዕከል የተለቀቁ የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን በማምጣትና በማላመድ የተሻሉትን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የተመረጡና በሄክታር እስክ 18 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ 3 የቡና ዝርያዎችን በይልማና ዴንሳ፣ ባህር ዳር ዙሪያና ሰሜን ሜጫ ወረዳዎች ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በቡና ተክል ካለሙት ግማሽ ሄክታር መሬት ባለፈው ዓመት 6 ኩንታል ጀንፈል ቡና ሰብስበው ለህብረት ስራ ማህበርና ለአካባቢ ገበያ አቅርበው በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት  ደግሞ  በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ   አርሶ አደር ክንዴ እንዳየሁ ናቸው።

አንዱን ኪሎ ጀንፈል በ170 ብር በማስረከብ ተጠቃሚ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ዘንድሮም አያያዙ የተሻለ በመሆኑ ከ8 ኩንታል ያላነሰ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ አስረድተዋል። 

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በቡና ከለማው መሬት ከ142 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በመሰብሰብ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለ ከግብርና ቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም