ቀጥታ፡

ለድንጋይ ከሰል የምርት ጥራት ስታንዳርድ ዝግጅትና የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ነው - የኢትዮጵያ ማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት

አዳማ  ፤ መስከረም 30/2016(ኢዜአ)፦  ለድንጋይ ከሰል የምርት ጥራት ስታንዳርድ የማዘጋጀትና ያለውን ሀብት ወደ ልማት ለማስገባት የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለፀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለፁት ከአምና ጀምሮ በሀገሪቷ የድንጋይ ከሰል ሁኔታና ደረጃዎች ላይ የተለያዩ ጥናቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በሀገሪቷ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ የድንጋይ ከሰል በብዙ ፋብሪካዎች ውስጥ ሊያገለግል እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን አመልክተዋል።

በምርቱ ላይ የሚስተዋለው የጥራትና የአቅርቦት ሰንሰለት ክፍተቶች መኖራቸውን የተናገሩት ዶክተር ጉታ፤ ችግሮቹን ለመፍታት የድንጋይ ከሰል ምርት ጥራት ስታንዳርድና ማኑዋል እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በድንጋይ ከሰል አመራረትና አጠቃቀም የዘርፉ የሰው ሃይል ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኝ ኢንስቲትዩቱ ከማዕድን ሚኒስቴርና ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም በግዥና የአቅርቦት ሰንሰለት መካከል ያለውን ክፍተት ለመፍታት እንዲሁም ውጤታማ የድንጋይ ከሰል አቅርቦት እንዲኖር እንደሚደረግ ተናግረዋል።

አሁን ያለው የድንጋይ ከሰል አቅርቦት ጥሩ ቢሆንም ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ፍላጎት አኳያ አናሳ መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የአምራቾች የአቅም ውስንነትና ተደራራቢ የማህበራት ወጪዎችን ደግሞ በምክንያትነት አንስተዋል።

ችግሩን ለመፍታትም የአምራች ማህበራትን አቅም ማሳደግና ያለባቸውን ተደራራቢ ወጪዎች የማስቀረት ስራ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ያዮና ካማሽን ጨምሮ ሌሎች ሀገሪቷ ያሏትን የድንጋይ ከሰል ሀብት በስፋት ወደ ልማት ለማስገባት የአዋጭነት ጥናት እየተከናወነ መሆኑንም ዶክተር ጉታ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የማዕድን ሀብት ልማት ክላስተር የማደራጀትና የማልማት ስራም ከዚሁ ጎን ለጎን እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም