ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነት ወደ ትግበራ ሊገባ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነት በቅርቡ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግሪን አፍሪካ ኢነርጂ ዓመታዊ ጉባኤና ‘የአፍሪካ የነዳጅ ሳምንት’ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ የአፍሪካ አገራት ሚኒስትሮች፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ለጋሽ ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ በከፍተኛ የውይይት መድረኮች ላይ እየተሳተፉ ነው።

ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ እየገጠሟት ካሉ ተግዳሮቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የኃይል ሽያጭ ዋጋ እንደሆነና በአፍሪካ ዝቅተኛ በሚባለው የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ እየሸጠች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የግሉን ዘርፍ በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የመንግስትና የግል አጋርነት የትብብር ማዕቀፍ ድንጋጌዎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በቀጣናዊ የኃይል ትስስር ላይ በትብብር እየሰራች እንደምትገኝና አሁን ላይ ለጅቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን ኃይል እየሸጠች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የተፈራረሙት የኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነትም በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ሕልውናቸውንና ዘለቄታዊ አገልግሎታቸውን ለማረጋገጥ እየሰራች ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን አብራርተዋል።

ጉባኤው እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ላይም ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በሚያዚያ ወር 2014 ዓ.ም የኃይል ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

በስምምነቱ መሰረት በመጀመሪያ ዙር 100 ሜጋ ዋት ኃይል ማቅረብ ሲሆን በሂደት ደግሞ መሰረተ ልማትን በማጠናከር የሽያጭ መጠኑን በየደረጃው ወደ 400 ሜጋ ዋት ለማሳደግ ታቅዷል።

የኃይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን በሁለቱ አገራት በኩል በማከናወን በሶስት ዓመታት ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል ለደቡብ ሱዳን ተደራሽ የሚደረግም ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም