ቀጥታ፡

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ "የመከላከያ ሠራዊት ስትራቴጂክ ጥናት ጆርናል" አሳትሞ አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2016 (ኢዜአ)፦ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ "የመከላከያ ሠራዊት ስትራቴጂክ ጥናት ጆርናል" አሳትሞ አስመረቀ።

የታተመው ጆርናል የኢትዮጵያን ታሪኮች እየሰነደ፣ የሀገር ፍቅር እሴትን በትውልድ ውስጥ ለማስረጽ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሠራዊት ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን፤ ጆርናሉ ዋር ኮሌጅ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ተወዳዳሪ የጦር ኮሌጅ የመሆን ውጤታማ ሥራው ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።


 

በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ለሕትመት የበቃው ስትራቴጂክ ጆርናሉ፤ ለሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የጦርነት ታሪኮችን የሰነደ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ፍልስፍና እና ስትራቴጂ ጥናት በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ገልፀው፤ መምሪያው ለጥናቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

"የኢትዮጵያ ወታደራዊ ፍልስፍና እና ስትራቴጂ" በሚል በተለያየ ጊዜ የነበሩ የጦርነት ታሪኮችን በመሰነድ በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙንም ነው የገለጹት።

መሰል ሰነዶች ለመጪው ትውልድ ትልቅ አሻራን የሚጥሉ በመሆናቸው ወታደራዊ ታሪኮች በአግባቡ ተሰንደውና ተደራጅተው ለቀጣይ ትውልድ መተላለፍ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። 

በቀጣይ የሚወጣው ጥናትም የሀገር ፍቅር ስሜትና ጀግንነት ለትውልድ ለማውረስ ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ነው የጠቆሙት።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ፤ ኮሌጁ ከመማር ማስተማርና የምርምር ተልዕኮው ባሻገር የምርምር ውጤቶችን ለመከላከያ ተቋማት ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።


 

በዕለቱ የተመረቀው የጥናት ጆርናልና በሂደት ላይ ያለው "የኢትዮጵያ ወታደራዊ ፍልስፍና እና ስትራቴጂ ጥናት" ሰነዶች ለሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል።

በየዓመቱ የሚታተሙ የመከላከያ ጆርናሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በስፋት ተደራሽ እንዲሆኑ በዲጂታል አማራጮችም እንደሚታተም ነው የገለጹት።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ፤ ጆርናሉ ከሠራዊቱ ባሻገር ለፖሊሲ አውጪዎችም ትልቅ ግብዓት ይሆናል ብለዋል።


 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም