በአገር አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ጤና ሕክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት ቁጥር እያደገ መጥቷል - ዶክተር ሊያ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
በአገር አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ጤና ሕክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት ቁጥር እያደገ መጥቷል - ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2016 (ኢዜአ)፦ በአገር አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ጤና ሕክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት ቁጥር እያደገ መምጣቱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
በዘርፉ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በዓለም ለ32ኛ ግዜ ታስቦ የሚውለው የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን "የአዕምሮ ጤና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና ሕክምና ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን ላይ ከ70 በመቶ በላይ ሆስፒታሎች ሕክምናውን እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ በተለያዩ የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር ብቁና ተወዳዳሪ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት ከትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የአዕምሮ ጤና ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን መገለል መከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን በበኩላቸው የአዕምሮ ጤና ቀንን አስቦ ከማዋል ባለፈ ዘላቂነት ያለውና የተቀናጀ የግንዛቤ መፍጠር ስራ ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።
ከመሪ ቃሉ ጽንሰ ሀሳብ በመነሳትም የአዕምሮ ጤና የሰብዓዊ መብት መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።
የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን እ.አ.አ 1992 ጀምሮ በየዓመቱ ኦክቶበር 10 በመከበር ላይ ይገኛል።
ዕለቱ በዓለም ዙሪያ የአዕምሮ የጤና ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠርና ለአዕምሮ ጤና ስራዎች ድጋፍ የማሰባሰብ ስራዎችን በማከናወን ታስቦ እንደሚውል የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
የባህሪና የስሜት መለዋወጥ፣ የነርቭ ስርዓት መዛባትና ሌሎች ተጓዳኝ ምክንያቶች አዕምሮ ላይ የሚደርሱ እክሎች እንደ አዕምሮ ጤና መታወክ ወይም ችግር እንደሚቆጠሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የአዕምሮ ጤና ችግር በአብዛኛው በወጣትና ታዳጊ የእድሜ ክፍል ላይ የሚገኙ ሰዎችን እንደሚያጠቃ የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያዎቹ ሰዎች በጊዜ አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል ካደረጉ መዳን እንደሚችሉ ይመክራሉ።