የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ10 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ፓኬጅ ቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ10 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ፓኬጅ ቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪዎቹ ዓመታት በአዲስ አበባ በኩል የሚያልፉ ከ10 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች የኢትዮጵያን የመስህብ ስፍራዎች እንዲጎበኙ የተለያዩ ፓኬጆች ቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን ገለጸ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ስራ ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ከሚያልፉ ዓለም አቀፍ መንገደኞች መካከል 65 በመቶ ያህሉ ወደ ከተማ ሳይገቡ የሚሄዱ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ይህን በመቀየር መንገደኞቹ ባላቸው አጭር ቆይታ አዲስ አበባን ጎብኝተው እንዲወጡ ''ስቶፕ ኦቨር አዲስ'' የተሰኘ የቱሪስቶች ማቆያ ፓኬጅ በመቅረጽ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተተገበረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በዚህም መንገደኞች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የተገነቡና ሌሎችም የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመጎብኘት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
አየር መንገዱ በ2035 ለማሳካት እየተገበረ በሚገኘው ስትራቴጂክ እቅዱ ከ10 ሚለዮን በላይ መንገደኞች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አቅዶ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት አቶ ለማ።
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ከማስፋት ባሻገር ቱሪዝምን እንደ አንድ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ''የቡና ቱሪዝም'' የተሰኘ አዲስ ፕሮግራም ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱንና በዚህም የቱሪስት ፍሰት እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።
በየሀገራቱ የሚገኙ የአየር መንገዱ ወኪሎችም መንገደኞች በኢትዮጵያ በኩል ሲያልፉ የመስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ የማድረግ ልዩ ተልዕኮ ይዘው በመስራት ላይ ናቸው ብለዋል።
ለአብነትም በኮሪያ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ህንድ፣ ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ወኪሎች ውጤታማ ስራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኮሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤሪያ ማኔጀር አቶ ምህረተአብ ተክላይ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ኮሪያዊያን በብዛት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል አዲስ አበባን እንደ መተላለፊያ በመጠቀም ወደ እስራኤልና ሌሎች መዳረሻዎች እንደሚጓዙ ያወሳሉ።
በአሁኑ ሰዓት ተጓዦቹ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ በተቀረጸው ፕሮጀክት ውጤት መገኘቱን ለአብነትም፤ በሳምንቱ 32 መንገደኞች አዲስ አበባን ጎብኝተው እንዲወጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚያልፉ ተጓዦች አዲስ አበባና ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችን እንዲጎበኙ የማድረግና የጎብኚዎችን ቁጥር የመጨመር ተግባር በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰጠውም የአየር መንገዱ አመራሮች ተናግረዋል።