በአዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብር ከ56 ሺህ በላይ ህጻናትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብር ከ56 ሺህ በላይ ህጻናትን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። 

አዲስ አበባ በቀደማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብር ያላትን ልምድ ለክልሎች ያካፈለችበት መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በመዲናዋ ህጻናት በአካል፣ በሥነ ልቦናና በእወቀት የተሟሉ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስችል የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብር እየተተገበረ ነው። 

ወላጆች እና አሳዳጊዎች ልጆች ሲያሳድጉ መከተል ስለሚገባቸው መንገዶች ምክር መስጠት፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ላይ በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የህጻናት መጫወቻ ቦታዎችና መዋዕለ ህጻናት ማስፋፋት እንዲሁም የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብርን ለማሳለጥ የሚረዳ ልህቀት ማዕከል መቋቋም ላይ ትኩረት መደረጉንም አብራርተዋል። 

በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህጻናትን በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙን የተናገሩት ከንቲባዋ፤ ለዚህም ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

እንደ ከንቲባዋ ገለጻ 2 ሺህ 500 ባለሙያዎች በማሰልጠን በልጅ አስተዳደግ ዙሪያ ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ ለወላጆችና አሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል።

ከዚህ ባለፈም ከ9 ሺህ በላይ ወላጆችና ህጻናት አልሚ ምግቦችን በቀጥታ እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች። 


 

በከተማ ደረጃ 56 ጤና ጣቢያዎችና 46 የቅድመ መጀመሪያ ትምህርት ቤቶች መርሃ ግብሩን በተሟላ መንገድ እየተገበሩት መሆኑንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ 152 የህጻናት መዋያ ቦታዎች ተገንብተው እና አስፈላጊው ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን 150 የህጻናት መጫወቻ ቦታዎችም ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።

የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብርን የበለጠ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የልህቀት ማዕከሉ በጉሌሌ እጽዋት ማዕከል እንደሚቋቋም ጠቁመው፤ ማዕከሉ ለመምህራንና ጤና ባለሙያዎች ስልጠና የመስጠትና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እንደሚያከናውን ነው የተናገሩት።

ከንቲባ አዳነች እንዳሉት፤ የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብር ተግባራዊ በተደረገባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ በመዲናዋ 56 ሺህ ህጻናትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።  

የጤና  ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በኢትዮጵያ  በጤናው  ዘርፍ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች  የሆኑ ህጻናትን ሞት በመቀነስ በኩል አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

ልጆች በአካልም በስነ ልቦናም የተሟላ ጤና ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ ላይ አሁንም የበለጠ መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት። 

በአዲስ አበባ ደረጃ በጤና ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ለሚመጡ እናቶችና አሳዳጊዎች ስለ ልጅ አስተዳደግ፣ መከተል ስለሚገባቸው  መንገዶች የምክር አገልግሎት  እየተሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልልም በ90 የጤና ተቋማት  ላይ የምክር አገልግሎት  መጀመሩን ገልጸው፤ በቀጣይ በሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል። 

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ  በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ የልጆች ስነ ልቦናና ዕድገት ላይ ጫና የሚያሳድሩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመከላከል ከባለድርሻዎች ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተቋማት ውስጥ የልጆች መዋያ ቦታ በማስፋፋት በኩል  አበረታች ጅምሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል። 

የትምህርት  ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብርን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ሚኒስቴሩ የበኩሉን  ሚና እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

የቀዳማይ ልጅነት ልማት መርሃ ግብርን ወጤታማ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም